Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ጋር ተወያይተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተመራ የልኡካን ቡድን በትናትናው ዕለት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጉ የሚታወስ ነው።

በጉብኝቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽና በሌሎች ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አንስተዋል።

“ኢትዮጵያ እና ሱዳን አንድ ህዝብ፤ አንድ ቤተሰብ ነን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ከህዳሴ ግድብ እና ከድንበር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮች ተከታታይነት ባላቸው ውይይቶች የሚፈቱ ናቸው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ውይይቱን አስመልክቶ በፌስቡክ ገፃቸው ባወጡት መረጃም፥ “ዛሬ በካርቱም ባደረግነው ውይይት ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላትን አጋርነት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በድጋሚ አረጋግጨላቸዋለሁ” ብለዋል።

“የሁለትዮሽ ትሥሥራችንን ለማጠናከር ያሉንን ሰፊ አማራጮች በምንፈትሽበት በዚህ ወቅት፣ ለኢኮኖሚያዊ ትብብር፣ የጋራ እድገት እና ቀጣናዊ መረጋጋት ያለን ቁርጠኝነት ይቀጥላል” ሲሉም ገልፀዋል።

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክም በውይይቱ ላይ፥ ኢትዮጵያና ሱዳን ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት እንዳላቸው በመጥቀስ፤ ግንኙነቱ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን ሱዳን እንደምታከብር ጠቁመው፤ በግድቡ ዙሪያ ያሉ ጉዳዮች በድርድርና ውይይት መፈታት እንዳለባቸውም አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በካርቱም ቆይታቸው ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሌተናል ጄነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን ጋርም ተወያይተዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.