Fana: At a Speed of Life!

ወ/ሮ አዳነች በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ በህግ ጥላ ስር የሚገኙ ተጠርጣሪዎች የሚገኙበትን ሁኔታ ተዘዋውረው ተመለከቱ

አዲስ አበባ ፣ሐምሌ 25 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ዛሬ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ በህግ ጥላ ስር የሚገኙ ተጠርጣሪዎች የሚገኙበትን ሁኔታ እና የተጠርጣሪዎችን አያያዝ በማረፊያቸው ተዘዋውረው ተመለከቱ።

ጠቅላይ አቃቤ ህጓ በህግ ጥላ ስር የሚገኙት አቶ ጃዋር መሃመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ እስከንድር ነጋን ጨምሮ ከእነርሱ ጋር የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ የሚገኝበትን ሁኔታ ነው ተዘዋውረው የተመለከቱት።

በምልከታቸውም ተጠርጣሪዎችን በተናጥል ጭምር በማናገር ስላሉበት ሁኔታ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸው ላይ ከማረፊያና ከፖሊስ አያያዝ ጋር ያለው ሁኔታ ጥሩ መሆኑን ተጠርጣሪዎቹ እንዳነሱላቸው ነው ወይዘሮ አዳነች የተናገሩት።

ከቤተሰብ ጥየቃ፣ ምግብ እንዲገባላቸው ከማድረግ እና ከጠበቆቻቸው ጋር ያላቸው ግኑኝነት ጋር ተያይዞ ያለው ሁኔታም እንደተሻሻለ አረጋግጠውልኛል ብለዋል።

የፀሃይ መሞቂያ ሰዓት እንዲስተካከል እና ቴሌቪዥን ወይም ሬዲዮ እንዲገባላቸው መጠየቃቸውን ጠቁመው÷ ጥያቄያቸው ታይቶ እንዴት እንደሚመለስ ከፌደራል ፖሊስ ጋር መግባባት ላይ እንደተደረሰ አመልክተዋል።

በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ስፍራውን መጎብኘታቸውንም እንደተረዱ አስታውቀዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራልና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ዘላለም መንግስቴ የምርመራው ሂደት ሁሉንም የተጠርጣሪዎችን የሰብዓዊ መብት ባከበረ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በአዳነች አበበ

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.