Fana: At a Speed of Life!

ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት ሂደት አመራሮች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው – አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 12 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግሥት ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት በሚያደርገው ጥረት በየደረጃው ያሉ አመራሮች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ ገለጹ።
ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች “አገራዊ ሪፎርም ለጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ” በሚል መሪ ሐሳብ ሥልጠና መስጠት ተጀምሯል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት በሚያደርገው ጥረት በየደረጃው ያሉ አመራሮች ሃለፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
መንግሥት እያደረገ ባለው ለውጥ ተቀዳሚ ተግባሩ ገለልተኛና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት መሆኑንም አብራርተዋል።
ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ደግሞ ህገ-መንግሥቱና የፌዴራል ሥርዓቱ ውጤታማና ጤናማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ እንዲሆን ያስችላል ነው ያሉት ።
ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ በዴሞክራሲ እጦትና የአብሮነት እሴቶች እየተሸረሸሩ በመምጣታቸው ዜጎች ለከፋ ችግር ሲዳረጉ ቆይተዋል ብለዋል።
ዜጎች በማንነታቸው አድሎ እየደረሰባቸውና እኩል የህግ ጥበቃና ከለላ ባለማግኘታቸው ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመሆኑም ዜጎች በህግ-መንግሥቱ የተጎናጸፏቸው መብቶች ሳይሸራረፉ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲተገበሩ ጠንካራ ተቋማትን መፍጠር ይገባል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያለ አመራር ሚና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንን ማስተካከል የሚቻለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ሲዳብርና የተቋማት ግንባታ በሚፈለገው ደረጃ ሲተገበር እንደሆነም አመልክተዋል።
የዛሬውም ሥልጠና አመራሮች ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡና እየተካሄደ ያለውን የሪፎርም አጀንዳ በሚገባ እንዲረዱ ነው ብለዋል።
ምክር ቤቱ 15ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ቀን እንዲሁም በወቅታዊ ጉዳይና አገራዊ ሪፎርሙን በማስመልከትም ሥልጠና በመስጠት ላይ ነው።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት በተዘጋጀው ሥልጠና የክልልና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶችና የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊዎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.