Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ ለ125ኛው የዐድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የዐድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የጀግንነት፣ የሀገር ፍቅር ስሜትና የጦርነት ጥበብ ውጤት ነው፡፡ ጎራዴ ታጥቆ መድፈኛን ለመጣል ከመንደርደር የበለጠ ጀግንነት የለም፡፡ ልዩነትን ወደ ጎን ጥሎ በጋራ ለአንድ ሀገር ግንባርን ለባሩድ፣ አንገትን ለካራ ከማቅረብ በላይ የጠለቀ የሀገር ፍቅር ከየትም አይመጣም፡፡ ሰፊ ጊዜ ወስዶ ራሱን በሴራና በስትራቴጂ ሲያዘጋጅ እና ከሌሎች በሚያገኘው እገዛ ሲደራጅ የከረመ ኃይልን ጥቃት መከቶ መልሶ በማጥቃት ማሸነፍ በቀላል ብልሃት የሚሆን አይደለም፡፡

በደምና በላብ የወዛ፣ በሥጋና በአጥንት የቆመ፣ በጥበብና በመደመር የደመቀ የዐድዋ ድላችንን እኛ ለኢትዮጵያውያን የተለየ ትርጉም ሰጥተን እንድናከብረው የሚያደርጉን ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ መሐል አንዱ፥ የዐድዋ ድል ሀገራችንን ማንም ሊያወርዳት ከማይችልበት ከፍታ ላይ የሰቀላት በመሆኑ ነው። ሀገራችንን ከዚህ ከፍታ ላይ ገፍትሮ ለመጣል ባለፉት ብዙ ዘመናት አያሴ ጥረቶች ተደርገዋል። በቅርቡ ታሪካችንም እንዲሁ፡፡ ግን አልተቻለም፡፡

ኢትዮጵያን ለመከፋፈልና ለማለያየት፣ ለማበጣበጥና ለማባላት፣ የተደረጉት ሙከራዎች ሁሉ የከሸፉት በዚህ የተነሣ ነው፡፡ ዐድዋ በከፍታ ላይ ከሰቀላቸው የኢትዮጵያ ዕሴቶች አንዱ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ነው፡፡ ከምዕራብና ከምሥራቅ፣ ከሰሜንና ከደቡብ የዘመቱ፤ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በመልከና በሞያ ኅብር የሆኑ፤ ነገር ግን ኢትዮጵያን ከቅኝ ግዛት የማዳን የእንድነት ዓላማ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ያስገኙት ድል ነው፡፡ በዐድዋ ዘመቻ ከ10 ዓመት ሕጻን እስከ 90 ዓመት አዛውንት ተካፍለዋል። ማየት የቻሉት ብቻ ሳይሆኑ ዓይነ ሥውራንም ዘምተዋል፡፡

ሴቶች ከስንቅ አዘጋጅነት እስከ ጦር መሪነት ተሰልፈዋል። የእስልምናና የከርስትና የሃይማኖት አባቶች ከጸሎት እስከ ግንባር ተሳትፈዋል። አዝማሪዎች በአንድ በኩል የሠራዊቱን ሞራል እየገነቡ፣ በሌላ በኩል ታሪኩን በግጥምና በዜማ እየከተቡ ዘምተዋል። ሌላው ቀርቶ ሽምጥ ጋላቢዎቹ ፈረሶቻችን በወኔ እሳቱ መሐል ሲገኙ፣ የጭነት አጋሰሶች በፈርጣማ ትከሻዎቻቸው ስንቅ ተጭነው፣ ሌሎችም እንስሳት መሥዋዕት ሆነው ዐድዋን የድል ቦታ፣ ኢትዮጵያን የድል ባለቤት አድርገዋል፡፡

ዛሬ በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ብንገባ፣ የትኛውንም የብሔር ብሔረሰብ ታሪከ ብናጠና፣ በየትኛውም የሀገሪቱ አቅጣጫ ሄደን ብንጠይቅ፣ ኢያየቶቹ ወደ ዐድዋ ያልዘመቱ ሕዝብ አናገኝም፡፡ መንገድና መገናኛ ባልተስፋፋበት፣ ዘመናዊ መጓጓዣ ባልነበረበት በዚያ ዘመን፣ ከመቶ ሺህ በላይ ሠራዊት ጫካዎቹንና ተራሮቹን በእግሩ እያቋረጠ የመጣው ኢትዮጵያን ብሎ ነው። መንግሥታዊ ሥርዓቱ ተመችቶት፣ አገዛዙ ተስማምቶት አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል፣ አያት ቅድመ አያቱ የነገሩት ሀገር ስለተነካችበት ነው፡፡ በትራንስፖርትና በመገናኛ አጥረት ሀገሩን ዞሮ ባያያትም፣ ሁሉም ግን ሀገሩ በልቡ ነበረች፤ ኮርታና ታፍራ የኖረች ብርቅዬ ሀገሩ በደም ሥሩ ውስጥ ትዘዋወራለች፡፡

ይህ ሁሉ ኅብረ ብሔራዊ ሠራዊት የተለያየ ቋንቋ እየተናገረ፣ የተለያየ እምነት እያመነ፣ የተለያየ ዓይነት ምግብ እየተመገበ፣ የተለያየ ዓይነት ልብስ ለብሶ፣ የተለያየ ዓይነት ባህል ይዞ፣ በምን እየተግባባ ዘመተ? የሚለውን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የተግባባው በኢትዮጵያዊነቱ ነበር። ኢትዮጵያዊ ኅብረ ብሔራዊነታችን መግባቢያ ቋንቋ ነውና፡፡ አንድነታችን የሚሠራበት ሰበዝ፣ ጥንካሬያችንን የሚገነባው ቅመም፣ ውበታችን የሚኳልበት ቀለም የሚቀዳው ከሌላ ሳይሆን ከኅብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነታችን ነውና።

ልዩነትን የማግባቢያ ፍቱን መድኃኒቱ የላቀ ዓላማ መሆኑን የዐድዋ ዐርበኞች ነግረውናል።፡ ማንም ከማይደርስበት ማማ ላይ የሰቀሉት ሌላው ዕሴታችን ይሄ ነው፡፡ ከግል ጥቅም፣ ከራስ ዝናና ከጊዜያዊ ሥልጣን የበለጠ፣ ዘለዓለማዊ የሆነ፣ ትውልድን የሚታደግ፣ ሀገርን የሚገነባ፣ የላቀ ዓላማ ካለ ልዩነቶች ሁሉ ውበት ብቻ ሳይሆኑ ጥንካሬ መሆናቸው የዐድዋ ዐርበኞች አስመስከረዋል። ልዩነቶች ለሀገር አንድነትና ለሕዝቦች መስተጋብር ፈተናዎች የሚሆኑት ሊያግባባቸው የሚቸል የላቀ ዓላማ ከሌለ ብቻ ነው፡፡

የዐድዋ ዘመቻ ኢትዮጵያውያንን ከጥንቱ በተሻለ ያስተሣሠረ ዘመቻ ነበረ። ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን፣ ከሁሉም ብሔሮች፣ ከሁሉም እምነቶች፣ ከሁሉም ዓይነቶች ለአንድ ዓላማ፣ በአንድ ቦታ በዚህ መልኩ መገናኘታቸው ያጠራጥራል። ይብዛም ይነሥም ዛሬ ያለችውን ኢትዮጵያ የሚወከሉ ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ከፍሎች ወረኢሉ ላይ ተገናኝተዋል። ዐድዋ ላይ ዘምተዋል። ለዚህም ነው ብዙ ምሁራን ዐድዋ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መሠረት ነው የሚሉት፡፡ እኛ ሁላችን የዐድዋ ልጆች ነን የምንለውም ለዚህ ነው፡፡

በውጊያው ጊዜ ከቅድመ አያቶቻችን መካከል አንዳቸው ጎድለው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ዐድዋም፣ የዐድዋ ልጅነትም ከእናካቴው ባልኖሩ ነበር። የሀገርን ጥሪ እኩል ሰምተው በጋራ ባይዘምቱና ዐድዋ ላይ የድል ሰንደቅ ባይተከሉ ኖሮ፥ ዛሬ የምናከብረው የድል ቀን መሆኑ ቀርቶ እንደሌሎች አፍሪካውያን የነጸነት ቀን በሆነ ነበር። በድል ቀንና በነጻነት ቀን መካከል የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት አለ። ዐድዋ ከእኛ የድል ሰንደቅነት አልፎ ተርፎ ለብዙ የነጻነት ቀኖች እንደ ምንጭ ሆኖ ያገለገለ፣ ለጸረ ቅኝ አገዛዝ እንቅስቃሴዎች ፋና የለኮሰ፣ በሁለት ዘሮች በጥቁሮችና በነጮች መካከል የተገነባውን የበታችነትና የበላይነት ግንብ የፈረካከሰ፣ ባለ ብዙ መልክ ትዕምርት ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ብዙ ጥፋቶችን ይታገሣሉ፡፡ መሪዎችና ቡድኖች የሚፈጽሟቸውን ስሕተቶች ይታገሣሉ፡፡ የመታረሚያና የመስተካከያ ጊዜ ይሰጣሉ። የመሪዎችና የቡድኖች ስሕተቶች ሀገራቸውን እንዲያፈርሱ ግን አይፈቅዱም፡፡ ይሄን የኢትዮጵያውያን ዕሳቤ የማይረዱ አካላት ተደጋጋሚ ስሕተት በታሪከ ውስጥ ሠርተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ነገሮችን ሲታገሥሠ የደከሙ፤ የተከፋፈሉ፤ አንድ ሆነው መቆም የማይችሉ ይመስሏቸዋል፡፡

በዐድዋ ዘመቻ ጊዜ ጣልያኖች ይሄንን ስሕተት ሠርተውታል። በኢትዮጵያ የአካባቢ መሪዎች መካከል የነበረው ትግል የሕዝቡ መለያየት የፈጠረው መስሏቸዋል፡፡ ሕዝቡ ነገሮችን በትዕግሥት እየተመለከታቸው መሆኑን አላወቁም፡፡ የመሪዎቹ እና የቡድኖቹ ስሕተቶች ሀገር የሚያፈርስ መስሎ ሲሰማው እንደ በረሐ ንብ ሆ ብሎ ተነሥቶ ሀገሩን እንደሚያድን አላወቁም፡፡

በቅርቡም ጁንታው የጣልያንን የመቶ ሃያ አምስት ዓመት ስሕተት ደግሞ ተሳስቷል። ኢትዮጵያውያን በትዝብት ዝም ሲሉ፤ ጥቂቶች በየሚዲያው ኃይለ ቃል ሲወራወሩ፤ እዚህም እዚያም በሚፈጠሩ ግጭቶች ወገኖቻችን መከራ ሲቀበሉ፤ ውጥረት የነገሠ ሀገር የተተራመሰ ሲመስለው – ኢትዮጵያን የማፍረሻ ጊዜው አሁን ነው ብሎ ተነሣ፡። ኢትዮጵያውያን ጁንታውን የታገሥት የመታረሚያና የመስተካከያ ጊዜ ለመስጠት መሆኑን ረሳው።፡

‹ሲተኙ እንደ ሬሳ፣ ሲነሱ እንደ አንበሳ› የተባለላቸው መሆናቸውን ዘነጋው፡፡ ሀገራቸው አደጋ ላይ ወደቀች መሆኑን ሲያረጋግጡ ሁሉን ነገራቸውን ትተው፣ በኢትዮጵያዊነታቸው ተግባብተው እንደሚዘምቱ አላወቀም፡፡ የሆነው ግን ይሄው ነበር። ዐድዋ የዕርቅንና የይቅርታን ኃይል ያሳየ ድል ነው፡፡ በየአካባቢው በነበሩ ግጭቶችና ውጊያዎች የተቀያየሙ መሪዎች ነበሩ፡፡ ጣልያኞችም እነዚህን ቅያሜዎች አስፍተው ኢትዮጵያውያንን ማንበርከክ እንደሚቸሉ ገምተው ነበር።

ሂሳባቸው ግን የተሳሳተ መሆኑን ያወቁት ወዲያው ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ቅሬታቸውን በዕርቅ ቅያሜያቸውን በይቅርታ ሻሩት። ‹ሁሉም ከሀገር አይበልጥም› በሚለው የኢትዮጵያውያን የቆየ መርሕ መሠረትከመንግሥት ጋር የተጣሉት ሳይቀሩ ለሀገራቸው ለመሞት መጡ፡፡ ሀገርና መንግሥት የተለያዩ መሆናቸውን የሚያውቁት ኢትዮጵያውያን፣ ሀገርን የሚያድነው ዕርቅና ይቅርታ መሆናቸውን አምነው ንቃቃቱን ዘጉት፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች አኩርፈው የሸፈቱ ሳይቀሩ ዕርቅና ሰላም እያወረዱ ከዐድዋው ዘማች ጋር ተቀላቅለዋል ዐድዋ የኢትዮጵያውያን የአመራር ጥበብ የታየበት ድል ነው፡፡ ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ በአራት መንገድ ሠራዊቱን አደራጅተዋል። የኋላ ኋላ ዕውን የሆነው ድል በአንድ ጀንበር የመጣ ድል አልነበረም፡፡ ብርቱ የሀገር ልጆች በተለያዩ መንገዶች መሣሪያ በማሰባሰብ፣ ስንቅ በማዘጋጀት፣ ጥቂት ጊዜ መግዛት የሚያስቸል የዲፕሎማሲና በመረጃዎች የመራቀቅ ሥራዎችን በማከናወን እና ሠራዊቱን አደራጅተው በመዝመት ያንን ድል አሳከተዋል።

በየምዕራፉ የነበረውን ፈተና በልኩ እየተጋፈጡ፣ ጥቃቅን ችግሮችን እየታገሠ፣ በጸና ዲስፕሊንእየተመሩ፣ ብልጫ ሊገኝበት የሚቻልበትን መንገድ እየተጠቀሙ፣ የጠላት ጓዳ ጎድጓዳ ውስጥ ገብቶ ጠቃሚ መረጃዎችን እየመነተፉ በመታገል የተገኘ ድል ነው፡፡ ይህ የመሪዎችን የአመራር ብልሃትና የሠራዊቱን መርሕ ጠባቂነት ያሳየ ነበር። የአመራር ብልሃት፣ የመሣሪያ አጠቃቀም፣ የሠራዊት ብቃትና የመልከአ ምድር አያያዝ ተባብረው ያስገኙት ድል ነው፡፡ በአጠቃላይ የዐድዋ ድል የማይቻል የሚመስለው የተቻለበት፣ የማይቀየረው የተቀየረበት ታሪካዊ ድል ነው፡፡

ያልዘመነ ጦር የታጠቀ አፍሪካዊ ኃይል ልዩ ልዩ የዘመኑ የጦር መሳሪያዎችን እስከ አፍንጫው የታጠቀ አውሮፓዊ ኃይል ድባቅ መትቶ የጣለበት ውብ አጋጣሚ ነው፡፡ የማይቀየር የሚመስለው የነጮች የበላይነት ታሪከ በጥቋቁር አናብስት የተሸነፈበት፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ጥቁር ፈርጥ ሆና ብቅ ያለችበት ድንቅ ጊዜ ነው፡፡

ዛሬ እንደ ተዓምር የምናያቸው ጉዳዮች፣ ከበለጸጉት ሀገራት ተርታ የመሰለፍ ጉዚችን በእርግጥም የሚሳኩ ስለመሆናቸው፣ የድህነት ታሪካችን በብልጽግና የማይሸነፍበት ምንም ምከንያት ስላለመኖሩ ከዐድዋ በላይ ምስከር ፈልጎ ማግኘት አይቻልም፡፡

እናም ኢትዮጵያን ለማበልጸግ የምንጓዝበት መንገድ ከዐድዋ ዕሴቶች መቀዳት አለበት። ዐድዋ ድል ብቻ አይደለም። ዐድዋ የኢትዮጵያ መለያ ‹ብራንድ› ነው። የኢትዮጵያውያን ከፍታ እንዴት ሊመጣ እንደሚችል የሚያሳይ ፍልስፍና ነው። ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከመተንተን ይልቅ ዐድዋን ማሳየት በሚገባ ለመረዳት ያስችላል። መሪና ተመሪ ተናቦና ተገናዝቦ ከሠራ ውጤቱ እንዴት ዓለምን እንደሚቀይር ዐድዋ የዘለዓለም ማሳያ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካና ለዓለም የሚተርፍ ሐሳብ እንዳለን ዐድዋ ትልቁ ምስክራችን ነው፤ ለወደፊትም ዐደዋን የመሰሉ፣ እንደ ዐደዋ የገዘፉ ምስክሮች እንደሚበዙልን አልጠራጠርም።

ጉዟችን ኢትዮጵያን ወደ ቀጣዩ ከፍታ ማሻገር ነው። የዐድዋን ሪከርድ መስበር ነው። እንደምንችል አረጋግጠናል፤ እንደምንችል ማሳየት ግን ይቀረናል። ሰንኮፎቻችን ሁሉ ቀስ በቀስ እየተነቀሉና መንሳፈፊያ ክንፎቻችን እየተዘረጉ ሲመጡ ያለ ጥርጥር ዘመናችን ብሩኅ ይሆናል፤ ጉዞውን ጀምረናል። ወደ ዐድዋ መድረሻው መንገድ ፈታኝ ነበር፤ የዐድዋ ድል ግን ጣፋጭ ነው። ወደ ብልጽግና መድረሻ መንገዳችን ፈታኝ ይሆን ይሆናል። ብልጽግናችን ግን እንደ ዐድዋ ሁሉ አይቀሬ ድል ነው። ኢትዮጵያ ከዐድዋ በታች አትወርድም። ከዐድዋ በላይ ወዳለው ከፍታ ደግሞ አንድ ሆነን እኛ እናወጣታለን።
መልካም የድል በዓል ለሁላችንም ይሁን።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.