Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ በሶስት የአፍሪካ ሀገራት ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀቁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በጊኒ ኮናክሪ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና በደቡብ አፍሪካ ያደረጉን ጉብኝት በማጠናቀቅ አዲስ አበባ ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጊኒ ኮናክሪ ቆይታቸው ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ጋር የተወያዩ ሲሆን በግብርና፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና ኢነርጂ ላይ የትብብር ሥራዎችን ለማስጀመር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ መዲና የሚገኘውን ኮናክሪ ወደብ መጎብኘታቸው የሚታወስ ነው፡፡

በኢኳቶሪያል ጊኒ ጉብኝታቸው ደግሞ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ቴዎዶር ኦቢያንግ ጋር በማላቦ ውይይት አድርገዋል።

በዚህም ሁለቱ መሪዎች በኢትዮጵያና በኢኳቶሪያል ጊኒ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የተወያዩ ሲሆን፥ በቱሪዝም ዘርፍ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ፕሬዚዳንት ኦቢያንግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ላከናወኗቸው ሥራዎች እና ጅማሬዎች አድናቆታቸውን በመግለጽ የሀገሪቱን ከፍተኛ የክብር ሜዳሊያ አበርክተውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሶስተኛ መዳረሻቸው በሆነው ደቡብ አፍሪካ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ካሳለፍነው ቅዳሜ ጀምሮ አድርገዋል።

በጉብኝታቸውም ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር በሁለትዮሽ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር በጤና እና በቱሪዝም መስክ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነትም ተፈራርመዋል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጆሐንስበርግ ከተማ ኢምፔሪያል ዎንደረርስ ክሪኬት ስታዲየም በመገኘት በሀገሪቱ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያውያን ዜጎች በደቡብ አፍሪካ ሁለንተናዊ መብታቸው ተከብሮ እንዲኖሩና ሕጋዊ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ለፕሬዚዳንቱ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ገልፀዋል።

በተጨማሪም በሀገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የሚደርስባቸውን ችግር ለመፍታት የሀገሪቱ መንግስት አበረታች ምላሽ መስጠቱን ነው የገለጹት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.