Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ በበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት የሰለጠኑ ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶችን አስመረቁ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሰላም ሚኒስቴር በበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ያሰለጠናቸውን ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶችን መርቀዋል፡፡

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደገለጹት፤ አሁን ያለው ትውልድ በነጻ መስጠት ከለመደ ኢትዮጵያ ብዙዎች አርዓያ የሚያደርጓት ትሆናለች።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት የኢትዮጵያ ምሰሶ ለመሆን ለተዘጋጁ ወጣቶች አድናቆታቸውን ገልጸው፤ “ከ100 ሚሊየን መካከል በነጻ የተሰጣችሁን ስለሆነ ከፍ ያለ ክብር ሊሰማችሁ ይገባል” ብለዋል።

ያደጉ ሃገራት በነጻ የሚያገለግሉ ዜጎች እንዳሏቸው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ዜጎች ሃገራቸውን መገንባት ችለዋልም ነው ያሉት፡፡

የሩሲያ ምሁራን ‘ድልና ስንፍና ተጋብተው ብዙ አይቆይዩም’ የሚል አባባል እንዳላቸው ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ድል ማስመዝገብ የሚፈልግ ከስንፍና መራቅ አለበት ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በነጻ ለማገልገል የተነሳሱት ወጣቶች ከስንፍና ለመራቅ ዝግጁ መሆናቸውን እንደሚያሳይ ገልጸው፤ “ዜጎች ትንሽ ጉልበት፣ ጥቂት ጊዜና ትልቅ ልብ ካላቸው ሃገር ይገነባል”ም ብለዋል ባስተላለፉት መልዕክት፡፡

ወጣቶቹ በሚሰማሩባቸው አካባቢዎች ብሔራዊ በጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠት የሚያስችላቸውን ስልጠና ላለፉት 45 ቀናት የወሰዱ ናቸው።

ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በፈቃደኝነት የተመለመሉት እነዚህ ሰልጣኞች ለቀጣይ 10 ወራት ከትውልድ ቀያቸው ርቀው በሁሉም የሃገሪቷ አካባቢዎች ተመድበው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ይቆያሉ ተብሏል።

ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት በቀጣይ ዙር እንደሚያካሂድ የሠላም ሚኒስቴር አስታውቋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.