Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ በአፍሪካ አገራት ያደረጉት ጉብኝት በኢቪዬሽን ዘርፍ ያለውን ትብብር ያሳድጋል- አቶ ተወልደ

አዲስ አበባ፣ጥር 5፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን በአፍሪካ አገራት ያደረጉት ጉብኝት ከአፍሪካ አገራት ጋር በኢቪዬሽን ዘርፍ ያለውን ትብብር ይበልጥ እንደሚያሳድገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሰለፍነው ሳምንት በጊኒ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ደቡብ አፍሪካ ያደረጉት የስራ ጉብኝት÷ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ትብብር ከማሳደግ አኳያ አስተዋጽኦ  እንደሚያበረክት የአየር መንገዱ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ገልጸዋል።

እኛ ትልቅ አየር መንገድ ነን አየር መንገዱ አፍሪካን በከፍተኛ ሁኔታ ያስተሳሰረ ነው፤ ትስስሩን መፍጠር ለሌሎች የአፍሪካ አየር መንገዶች ትልቅ ፈተና የሆነባቸው ጉዳይ ነው ብለዋል አቶ ተወልደ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የምዕራብ አፍሪካ አገራት አየር መንገድ የሆነውና መቀመጫውን በቶጎ ያደረገው ስካይ አየር መንገድ ለማላዊ፣ ሞዛምቢክና ኢኮቶሪያል ጊኒ አየር መንገዶች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

አየር መንገዱ በአሁኑ ሰአት የቻድ፣ ቶጎ፣ ማላዊ እና ሞዛምቢክ አየር መንገዶችን እያስተዳደረ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ከዛምቢያና ጋና አየር መንገዶች ጋር በትብብር ለመስራት ውይይት መጀመሩን ገልጸው÷አየር መንገዱ ከአፍሪካ አገራት ያለው ግንኙነት በውድድር ላይ ሳይሆን በትብብር መስራት ላይ ያተኮረ እንደሆነ  ገልጸዋል፡፡

የጊኒ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አልፋ ኮንዴ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጊኒ አየር መንገድን እንዲያቋቁም ጥያቄ አቅርበው እንደነበርና በአሁኑ ወቅትም አየር መንገዱን የማቋቋሙ ሂደት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን ገልፀዋል።

አገራቱ አየር መንገዱን ለማቋቋም ያደረጉት ስምምነት አፍሪካን ወደ አንድ ለማምጣትና የበለጠ ለማቀራረብ  ከማስቻል በላይ የኢትዮጵያንና ጊኒን ሁለትዮሽ ግንኙነትም ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።

የኢኳቶሪያል ጊኒ ርዕሰ መዲና ማላቦ አየር መንገዱ በአፍሪካ ካሉት የመዳረሻ ከተሞች አንዷ ናት።

አቶ ተወልደ ኢኳቶሪያል ጊኒ ባላት የነዳጅ ሀብት “የአፍሪካ ኩዌት” በማለት የገለጿት ሲሆን አገሪቷ አየር መንገድ ለማቋቋም ፈተና ሆኖባት እንደነበር አውስተዋል።

ያለፈውን አንድ ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአገሪቷ ፕሬዚዳንት ቲኦዶር ኦቢያንግ በቀረበ ጥያቄ መሰረት አየር መንገዱን የማቋቋምና የማስተዳደር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለቤትነቱ የደቡብ አፍሪካ መንግስት የሆነው የአገሪቷ ብሔራዊ አየር መንገድ በፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ በሚያከናውነው ስራ ትርፍ እያገኘ ባለመሆኑ  የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በህዳር ወር 2012 ዓ.ም የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

አየር መንገዱ ካለው ድርሻ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲገዛ ጥያቄ ካቀረበ አየር መንገዱ በጉዳዩ ላይ እንደሚያስብበት ገልጸው ነበር።

እንደ አቶ ተወልደ ገለጻ አየር መንገዱ ያለው ፍላጎት የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ወደቀድሞው ዝናው እንዲመለስ  መሆኑን ጠቁመዋል።

ናይጄሪያና ቶጎ ጎረቤት አገሮች ሲሆኑ በአውሮፕላን በረራ ከአንዱ አገር ወደ ሌላኛው አገር ለመሄድ የሚጀፈው 45 ደቂቃ ነው።

በሁለቱ አገራት መካከል የአየር በረራ ባለመኖሩ ከአንዱ አገር ወደ ሌላው አገር ለመሄድ በረራዎች የሚካሄዱት በለንደን በኩል መሆኑን ጠቅሰው ይህም የሰባት ሰአት የበረራ ጊዜ እንደሚፈጅ አቶ ተወልደ ይገልጻሉ።

አየር መንገዱ በቶጎ ሎሜ የአስካይ አየር መንገድ ስራ በማስጀመሩ ሰባት ሰዓት የሚወስደውን የአየር በረራ ጊዜ እንዳስቀረው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ እያከናወነ ያለው ስራ ሁሉም የአፍሪካ አየር መንገዶች የሚመኙት ዓይነት እንደሆነና ለአህጉሪቷም ትልቅ መነሳሳት የፈጠረ ነው ማለታቸውን ከኤዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ120 በላይ በኢትዮጵያ ደግሞ 22 መዳረሻዎች ሲኖሩት በፈረንጆቹ በ2019 12 ሚሊየን ተሳፋሪዎችንም አጓጉዟል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.