Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ዕርቅን ማውረድ ለቀጠናው ውህደት መሠረት ነው-ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ዕርቅን ማውረድ ለቀጠናው ውህደት መሠረት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለፁ።
 
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በጅቡቲ በተካሄደው የሶማሊያ እና በሶማሌላንድ ግንኙነት ዙሪያ ባተኮረው የምክክር መድረክ ላይ ተሳትፈዋል።
 
በዚሁ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ዕርቅን ማውረድ ለቀጠናው ውህደት መሠረት እንደሆነ መግለፃቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መረጃ አመላክቷል።
 
“ትብብር እና ሰላም በግንባር ቀደምነት ከተተገበሩ ውጤታማ በሆነ መንገድ የቀጠናውን ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል የተትረፈረፈ ሀብት አለ” ብለዋል።
 
“የድህነት እና የተስፋ መቁረጥን ዑደት ለመሻር ሃብታችንን ማሰባሰብ እንችላለን” ሲሉም ተናግረዋል።
 
በሶማሊያ እና በሶማሌላንድ ግንኙነት ዙሪያ በጅቡቲ የተካሄደው የምክክር ጉባኤው በየካቲት 2012 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ የተደረገው ውይይት ተከታይ ክፍል ነው።
 
በምክክር መድረኩ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የጅቡቱ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ እና የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሳ ቢሂ አብዲ እና የኢዳግ ዋና ፀሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተገኝተዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና የልዑካን ቡድናቸው በሶማሊያ እና በሶማሌላንድ ግንኙነት ዙሪያ በሚደረገው የምክክር መድረክ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ጅቡቲ መግባታቸውንም ይታወቃል።
 
#FBC
 
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.