Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክን መረቁ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፌደራል እና የክልሉ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት የአካባቢው ወጣቶች ስራን መልመድ፣ አሰሪን ማክበር እና ባጭር ጊዜም ከውጭ የተገኘን ልምድ በመተካት በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
የተመረቀው ፓርክ ከኢንዱስት ፓርክነት ባሻገር የመዝናኛ እና ለተማሪዎች የምርምር ማዕከል እንዲሆን የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ሊሰራ ይገባልም ነው ያሉት።
ሰዎች ካላዩት አይጠብቁትም፤ ካላዩት አይማሩትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቴክኖሎጂ እና እውቅት ሽግግር ከመጠቀም በተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የባህር ዳር ከተማ በተፈጥሯዊ ስጦታዎች የታደለች መሆኗን በመጥቀስም የጎብኚዎች መዳረሻነቷን ለማጠናከር የሰውን ጭንቅላት መጠቀም ይገባል ብለዋል።
እንዲሁም ኢንዱስትሪ ፓርኩን ለማልማት ከአካባቢው ለተነሱ አርሶ አደሮች ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ጋር በማያያዝ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው የሚመለከታቸው አካላት እንዲሰሩም የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተባበረ ክንድ በሀገሪቱ የተጀመረው ሁለንተናው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላው በክልሉ የማምረቻውን ዘርፍ ለማሳደግ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን እና እየተሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በፌደራል የኢንዱስትሪ ፓርኮች በኩል የባህር ዳር፣ ደብረ ብርሃን እና ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባታቸውን ጠቅሰው በክልሉ መንግስትም የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ መሆኑን አንስተዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ በኢትዮጵያ 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባታቸውን በመግለፅ ከእነዚህ ውስጥ 10ሩ ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
በሀገሪቱ ወደ ስራ የገቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ76 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቀጥተኛ የስራ እድል መፍጠራቸውን እና ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የስራ እድል መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።
ፓርኮች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሰራተኞችን ሳይቀንሱ ስራቸውን እንዲቀጥሉ እና ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ የሚውሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን እንዲያመርቱ መደረጉንም አውስተዋል።
ኢንዱስትሪ ፓርኩ ወደ ስራ ሲገባ ከአካባቢው ለተነሱ ዜጎች ቅድሚያ እንደሚሰጥም ገልፀዋል።
የባህር ዳር እና አካባቢው ነዋሪዎም የፓርኩ ዋነኛ ተጠቃሚ በመሆናቸው ፓርኩን እንዲጠብቁም አደራ ብለዋል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ፣ የብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱዓለምን ጨምሮ ሌሎች የክልል እና የፌዴራል ስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.