Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጎበኙ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 23 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጎበኙ።

በጉብኝቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይልን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ ያለበትን ሁኔታ ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን፥ የግድቡ የሲቪል እና ኤሌክትሮ መካኒካል የግንባታ ደረጃ ያለበትን ሁኔታ ገምግመዋል።

በዚሁ ወቅትም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሥራ ክንውን ሁኔታ ሪፖርት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ቀርቧል።

የክንውን ሁኔታውን በመመልከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ሕልምን እውን ለማድረግ ውጤታማ ሥራ የማከናወንን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል።

ከአያያዝ ጉድለት የተነሣ የተከሠተውን የሥራ መጓተት አስታውሰው፤ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የሕዳሴው ግድብ የግንባታ ሥራ የገጠመውን ችግር ለመፍታት መንግሥት የወሰዳቸውን ርምጃዎች ዘርዝረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፥ በፕሮጀክቱ የስራ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩት ኩባንያዎች “የዛሬው ጉብኝቴ ከዚህ ቀደም ካደረኩት የተሻለ አፈጻጸም ያየሁበት በመሆኑ አስደስቶኛል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ተስፋ የጣለበትን ይህን ፕሮጀክት እውን ለማድረግም በተናጥል ሳይሆን በህብረት እና በጋራል ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዚህም በቀጣይ አመት በሚያደርገው ጉብኝት ቢያንስ ሁለቱ ተርባይኖች ሃይል ሲያመነጩ ማየት እንደሚፈልጉም መልእክታቸውን ለኩባንያዎቹ አስተላልፈዋል።

በዚህ የግንባታ ሂደት ላይ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታትም መንግስታቸው ሌት ተቀን እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመለየት በጥራትይ እየተሰራ በመሆኑ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።

በዚህም በቀጣይ 2013 ዓ.ም ሁለቱ ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት ይጀምራሉም ብለዋል።

በይስማው አደራው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.