Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ ኢትዮጵያን መገንባት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ተናገሩ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 18 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ታላቅ ሃገር ሳይኖር ታላቅ ህዝብ ስለማይኖር ኢትዮጵያን መገንባት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በከምባታ ጠምባሮ ዞን ዱራሜ ከተማ በስታዲየም ለተሰበሰቡ ነዋሪዎች ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም ለግለሰብ ማህበረሰብ፤ ለማህበረሰብ ደግሞ ሃገር ታስፈልጋለች ብለዋል።

ከዚህ አንጻርም ሁሉም ሰው የራሱን ማንነት ይዞ ለጠንካራ ሃገር ግንባታ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

አያይዘውም አባቶቻችን በደምና በአጥንታቸው ያቆዩልንን ኢትዮጵያ ወደከፍታ ማውጣት የዚህ ትውልድ ሃላፊነት መሆኑን አንስተዋል።

ለውጡ አሁን ላይ ከየትኛውም ቦታ ፈተና ቢገጥመውም መንገዳችን መደመር ብቻ ነው መድረሻችንም ብልፅግና ነው ብለዋል በንግግራቸው።

በደሃ ሃገር ውስጥ የሚኖረው ደሃ ክልል፣ ዞን እና ወረዳ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ተባብረን ሰርተን የህዝባችን ህይወት መለወጥ ካልቻልን ለግል በሚገኝ ስኬት እርካታ ሊመጣ አይችልምም ነው ያሉት።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው በበኩላቸው፥ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ ህዝብ ከመንግስት ጎን እንደሚሆን ገልጸዋል።

የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በማጠናከርም ብልጽግናን እውን ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም አውስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ከስታዲየም ቆይታ በኋላ በአዳራሽ ከከምባታ ጠምባሮ ዞን ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ የመሠረተ ልማት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሁም የመንገድ ግንባታ ጥያቄዎች፣ የውሀ አቅርቦት እና የመጸዳጃ አገልግሎት ፍላጎት በተለይም ከወሊድ ጤና ክብካቤ ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ሴቶች በማኅበረሰባቸው ውስጥ ያላቸው ሚና ከፍ ይል ዘንድ፣ የሴት አመራሮች ቁጥር እንዲጨምር መንገድ መጥረጋቸውን አድንቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው በያዝነው ዓመት መጀመሪያ መንግሥት “የማጠናቀቅ ዓመት” የሚል ጭብጥን ተግባራዊ በማድረግ፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውሰዋል።

አንዱ ሌላውን ማድመጡ እና ሁሉም ሰው በሰውነቱ መከበሩ የልማት ወሳኝ መለኪያ መሆኑንም አንስተዋል።

በዞኑ የሚነሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት መንግስት እንደሚሰራ አስረድተው፥ እንደ ሃገር ሃብት መፍጠር ላይ ማተኮር እንደሚገባም አንስተዋል።

ከተነሱት ጉዳዮች ውስጥ የተወሰኑትን አስመልክቶ፣ የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ የኤሌክትሪክ መሥመር ሥራዎች በቅርቡ የሚከናወንባቸውን አራት ወረዳዎች ጠቁመው፣ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ በመላው ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲኖር ታቅዶ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያያዘም፣ በአካባቢው የሚገኙ ብዙ መንደሮችን የሚያዳርስ የውኃ ሥራ የትግበራ መርሀ ግብር ንድፍ እና ቀጣይ ፕሮጀክቶችን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊው አቶ ሀብታሙ ተገኔም እንዲሁ፣ የፌደራል መንግሥት በጀት የመደበላቸውን ቀጣይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በማመላከት፣ በያዝነው የበጀት ዓመት የሚጠናቀቁ መሆኑን አመላክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰዓት በኋላም ከሃላባ ዞን ነዋሪዎች ጋር ይወያያሉ።

በአላዛር ታደለ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.