Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ የሀላባ ሕዝቦች የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ለማድረግ እንዲሰሩ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 18 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሀላባ ሕዝቦች በኢትዮጵያ የነበራቸውን ታሪክ የሃገሪቱን ብልፅግና እውን ለማድረግ እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው እለት በቁሊቶ ስታዲየም ከሀላባ ዞን ለተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም የሀላባ ህዝቦች በኢትዮጵያ ታሪክ የነበራቸውን ጉልህ ሚና አስታውሰው፥ ይህን ሚና የሃገሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥ እንዲቀጠሙበት ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት ለሀላባ ህዝቦች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠውላቸዋል።

አያይዘውም ህዝቡ ጠንክሮ በመሥራት ወደ ፊት እንዲጓዝ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት “በሃገራችን ተገፋፍተን እና ተከፋፍለን አይተነዋል ያተረፍነው ድህነት ብቻ ነው” ብለዋል።

አሁን ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት አዋጩ የሰላም መንገድ መሆኑንም ነው ያመላከቱት።

ለዚህም በሰለጠነ መንገድ መወያየት፣ ልዩነቶችን ማክበር እና ከትናንት ተምሮ ለነገ በጥበብ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

እንደ ሀገር ረዥሙን መንገድ ተደላድሎ ለመሄድ ለተወሰነ ጊዜ ወገባችንን ጠበቅ አድርገን መስዋዕትነት መክፈል አለብንም ብለዋል በመልዕክታቸው።

በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በቁሊቶ ስታዲየም በመገኘት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት በማስመልከት እና መደመርን በማክበርም 120 በሬዎች እና 3 ግመሎችን በስጦታ መልክ አበርክተዋል።

በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀላባ ዞን ሀላባ ቁሊቶ ከተማ ከዞኑ ነዋሪ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ ከዞኑ ከሁሉም አካባቢዎች የተወከሉ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

ነዋሪዎቹ የመንገድ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የወረዳ መዋቅርን፣ የበርበሬ ማቀነባበሪያ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና የሆስፒታል ግንባታን የተመለከቱ ጥያቄዎች አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በምላሻቸው ዘላቂነት ባለው የውሃ ልማት መርሐ ግብር በሀገሪቱ ቆላማ እና ውሃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ውሃ ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

መንገድን በተመለከተ አስቀድሞ በተያዘ እቅድ መሠረት የሀላባ ሻሸመኔ መንገድ ዳግም ጨረታ ወጥቶለት በዚህ አመት ይጀመራል ብለዋል።

ሀላባ – ሲራሮ – ሻመና መንገድም ለቀጣይ አመት ዕቅድ ተይዞለታል ነው ያሉት።

በአጠቃላይ ከማህበረሰቡ ተነስተው በመንግሥት ምላሽ የሚሰጣቸው ጉዳዮች አቅም በፈቀደ መጠን እንደሚመለሱም አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስታቸው የህዝብን ችግር ለመፍታት ሳይታክት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በአላዛር ታደለ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.