Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ የሃይቅ- ቢስቲማ – ጭፍራ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን በይፋ አስጀመሩ

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሃይቅ- ቢስቲማ- ጭፍራ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን በይፋ አስጀመሩ።

በመርሃ ግብሩ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችም ተገኝተዋል።

የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱን በይፋ ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፥ አካባቢው በተፈጥሮ ሀብት የታደለ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም ግን ላለፉት ዓመታት የአካባቢው ነዋሪ ሲያነሳው የነበረው የመንገድ ጥያቄ መልስ ሳያገኝ በመቅረቱ ተጠቃሚ መሆን አልቻለም ነበር ብለዋል።

አሁን በዚህ መንገድ መሰራት አካባቢው ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆን እና በተለይም ከአፋር ክልል ጋር በሚኖረው ግንኙነት በኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን ከፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

የመንገዱ ግንባታ የአካባቢውን ማኅበረሰቦች ንግድና ማኅበራዊ ሕይወት በብዙ መልኩ የሚያቀላጥፍ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው፥ የረጅም ጊዜ የአካባቢው ህብረተሰብ ጥያቄ ጥያቄ ዛሬ በመመለሱ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

የመንገዱ መገንባት ለአካባቢው ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ የግንባታ ስራው የጀመረው መንገድ 74 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ርዝመት ይኖረዋል።

የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ከ2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል።

የመንገድ ግንባታው በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ለአመታት የቆየውን የህዝብ የልማት ጥያቄ በመመለስ ለአገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተነግሯል።

የመንገድ ግንባታውን የሚያከናውኑት ፓወርኮን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርና አሰር ኮንስትራክሽን በጋራ ሲሆኑ የግንባታው ወጪ የሚሸፈነው በኢትዮጵያ መንግስት እንደሆነ ታውቋል።

መንገዱ በአሁኑ ወቅት በጠጠር ደረጃ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን የአፋርና የአማራ ክልሎችን የሚያገናኝ ነው።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.