Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ለ1 ሺህ 441ኛው የኢድ አል አድሀ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1 ሺህ 441ኛው የኢድ አል አድሀ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ ሙሉ መልእክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ለዒድ አል-አድሐ በዓል እንኳን አደረሳችሁ

ለመላው ሙስሊም ወገኖቼና ለተቀረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ፣ እንኳን ለ1 ሺህ 441 ኛው ዓመተ ሒጅራ፣ ለታላቁ የዒድ አል-አድሐ / የዐረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን ለማለት እወዳለሁ። ዒድ ሙባረክ!

የዘንድሮው የዐረፋ በዓል በተለያዩ ምክንያቶች ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ለየት ያለ ትርጉም አለው፡፡ ከዓመታት ግንባታና የዲፕሎማቲክ ትግል በኋላ፣ የመጀመሪያውን የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ባሳካንበት ጊዜ የሚከበር በመሆኑ በዓሉን በከፍተኛ ሐሴት ውስጥ ሆነን ነው የምንቀበለው፡፡

ሙስሊሙ ወገናችን ከዓረቡ ዓለም ጋር ባለው የሃይማኖት፣ የባህልና የቋንቋ ትሥሥር ምክንያት ከመካከለኛው ምሥራቅና ከዓረብ ሀገራት ጋር በተያያዘ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለሚገጥሟት ልዩ ልዩ የዲፕሎማሲ ትግሎች ወሳኝ ሚናዎችን ሲጫወት ቆይቷል፡፡

የሕዳሴ ግድባችን እውን እንዲሆንም ገንዘብ ከማዋጣትና ጠቃሚ ሐሳቦችን ከማበርከት ባለፈ በዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎው ሂደት ግንባር ቀደም በመሆን የሁላችንም የሆነችው ሀገራችንን ለማኩራት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ሙስሊሞች መሥዋዕትነት መክፈላችሁን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በክብር ያየዋል፡፡

ላበረከታችሁት አስተዋጽዖ በኢፌዴሪ መንግሥትና በመላው ኢትዮጵያዊ ስም ሳላመሰግን አላልፍም፡፡

ዒድ አል አድሓ፣ በዓረብኛ “የመሥዋዕት በዓል” ማለት ሲሆን፣ ነቢዩ ኢብራሂም ለጌታው የነበረውን ፍጹም እምነት፣ በቆራጥነት ያሳየበት ልዩ ቀን ነው። ፈጣሪ አላህ፣ (ሱብሀነሁ ወተአላ) ልጅህን መሥዋዕት አቅርብልኝ ብሎ በጠየቀው ጊዜ ኢብራሂም አንድዬ ልጁን፣ እስማኤልን ወደ መሠዊያው ወስዶታል። ፈጣሪም የኢብራሂምን ፍጹም እምነት ተመልክቶ፣ ሙክት እንደሰጠውና በልጁ ምትክ ሙክቱ ስለተሰዋ የሚከበር በዓል ነው።

የገዛ ልጁን ለመሠዋት ዝግጁ ከመሆን የበለጠ ቆራጥነት የለምና፣ ዒድ አል-አድሐ “የመሥዋዕት በዓል” እየተባለ ይጠራል።

ከልጅ በላይ የቀረበና የሚወደድ ነገር እንደሌለ የወለደ ሰው ሁሉ ያውቀዋል፡፡ እንደ ኢብራሂም ያሉ መልካምና ቆራጥ ሰዎች፣ ለእምነታቸው ሲሉ አንድዬ ልጃቸውን መሥዋዕት ለማድረግ ይዘጋጃሉ። መልካም ሰዎች እንደ ኢብራሂም ናቸው፡፡ ለመልካም ዓላማ ሲሉ እጅግ ውድ የሆነ ሀብታቸውን፣ ልጃቸውን ሲሰጡ ቅር አይላቸውም፡፡

በተቃራኒው ክፉዎች ለእኩይ ዓላማቸው ወንድማቸው ላይ በትር ያነሳሉ፡፡ እህታቸው ላይ፣ ልጃቸው ላይ፣ እናትና አባታቸው ላይ ሲጨክኑ ዐይናቸውን አያሹም፡፡ ከእኛም መካከል አንዳንዶች ለተራ ቁሳዊ ሀብቶች፣ ለትንንሽ የፖለቲካ ድሎችና ለሥልጣን እኩይ ተግባራትን የሚፈጽሙ አሉ፡፡ ለሆዳቸው ሲሉ ቤተሰባቸውን፣ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ሀገርና ወገናቸውን ለመሸጥ ሲዘጋጁ እንደማየት የሚያሳዝን ነገር የለም፡፡ እንዲህ የሚያደርጉ አካላት ከክፉ ሥራቸው እንደሚለሱ ሕዝበ ሙስሊሙ በጥበብ እንዲያስተምራቸው አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡

የተከበራሁ ሙስሊም ወንድምና እህቶቼ፣እንደሚታወቀው የዒድ አል-አድሐ በዓል፣ ከአምስቱ የእስልምና መሠረቶች መካከል አንዱ የሆነውና ማንኛውም ሙስሊም የገንዘብና የጉልበት ዐቅሙ እስከፈቀደ ድረስ በሕይወት ዘመኑ ቢያንስ አንዴ ሊያከናውነው የሚገባው፣ የሐጅ ሥርዓት የሚፈጸምበትም ቅዱስ በዓል ነው። ያም ሆኖ የዘንድሮው የዐረፋ በዓል የሚከበረው ዓለምን እየፈተናት ያለውን የኮሮና ወረርሽኝ በምንዋጋበት ወቅት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በዓሉን ከዚህ ቀደም ካየናቸው በዓሎች ለየት ባለ መልኩ እንድናከብረው የሚገፋፉ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ለወትሮው በዐረፋ በዓል ሕዝበ ሙስሊሙ በጋራ ሆኖ ለማክበር ዘመድ ወደ ዘመዱ፣ ልጆች ወደ ቤተሰቦቻቸውና ወደ ሀገር ቤት መሄድ የተለመደ ነበር፡፡

ከዚህም ከፍ ሲል በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዓለም ሙስሊሞች የዐረፋ በዓልን ለማክበር ወደ ቅዱሱ ሥፍራ ወደ ሳዑዲ ይጎርፋሉ። ጥቁሩ፣ ነጩ፣ አፍሪካዊው፣ እስያዊው፣ አውሮፓዊውና ሌላውም ከያቅጣቸው ተሰባስቦ ዒድ አል-አድሐን በጋራ ሲያከብረው ኖሯል፡፡ ዘንድሮ ግን ነገሮች እንደቀድሞው ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ መሰባሰብን የማይፈቅድ፣ አካላዊ መቀራራብን የሚከለክል ወረርሽኝ በማጋጠሙ ምክንያት በዓሉን በጥንቃቄ እንድናከብረው ግድ ብሏል፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀው በአሁኑ ወቅት በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ፣ የሚታመሙና የሚሞቱ ወገኖቻችን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ነው። ይህ ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ መሆን አለበት። የትምህርታችንና የጸሎታችን ጉዳይ መሆን አለበት። ወረርሽኙን መከላከልን እንደ አንድ ሃይማኖታዊ ግዴታ ልንወስደው ይገባል። ወረርሽኙ የፈጠራቸውን ክፍተቶች ለመድፈን ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል፡፡

አቅማቸው ደከም ያሉ ወገኖቻችንን እንድንደግፍ፤ ማዕዳችንን እንድናጋራ፤ በዚህ ፈታኝ ወቅት ለተቸገሩ ወገኖቻችንን አልኝታቸው መሆናችንን እንድናሳያቸው ስል ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡ ዒድ አል-አድሐ የመሥዕዋትና የመዳን በዓል እንደመሆኑ መጠን ወደ ሐጅ የሚሄደው ሰው ብቻ ሳይሆን የማይሄደውም ጭምር ‹‹ኡድሒያ›› የማረድ ግዴታ እንዳለበት የእምነቱ አስተምሮ ያዛል፡፡ በዚህ አስተምህሮ መሰረት ለኡድሒያ ከሚታረደው አንድ ሦስተኛውን ለድኾችና ለተቸገሩ ወገኖቻችን በማካፈል በተለይም ይሄንን አስቸጋሪ ወቅት በስኬት እንደምንሻገረው አልጠራጠርም፡፡

በሌሎች አጋጣሚዎች እንደገለጽኩት፣ በዚህ ወቅት ማከናወን ከሚገቡን ሐገራዊ ተግባራት መካከል ሌላው ከሕዳሴ ግድብ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ቀሪ የሕዳሴ ግድባችን ሥራዎች ላይ እንድንረባረብና የአረንጓዴ አሻራችንን በስኬት እንድንወጣ ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡ አረንጓዴ አሻራችንን ከአሁኑ ማሳረፍ ካልቻልን የምንገነባው የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎቻችን ሁሉ እድሜ አይኖራቸውም።

ኢትዮጵያ አረንጓዴ ሀገር መሆን አለባት። ድርቅን የምትቋቋም፣ ምንጮቿ የማይነጥፉ፣ አራዊቷና አዕዋፏ የማይሰደዱ ሀገር መሆን አለባት። ይህ እንዲሆን ሕዝበ ሙስሊሙ ወሳኙን ሚና እንዲጫወት አደራ እላለሁ። በቀሪ የሕዳሴ ግድብ ግንባታና የዲፖሎማሲ ሥራዎች ላይ ርብርብ በማድረግ ቀጣዩ የዒድ አል-አድሐ በዓል ሲከበር ግድባችን እጅግ ከፍ ወዳለ ምእራፍ ተሸጋግሮ እንደሚሆን ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡

በድጋሚ ለመላው ሕዝበ ሙስሊም፣ እንኳን ለዒድ አል-አድሐ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ!

አመሰግናለሁ!!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.