Fana: At a Speed of Life!

ጡት ለማጥባት ምቹ የሆኑ ጤና ተቋማት ዕውቅና ተሰጣቸው

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ባለው ጤና ተቋማትን ለጡት ማጥባት ምቹ የማድረግ ኢንሼቲቭ ጥሩ አፈፃፀም ላሳዩ 14 የጤና ተቋማት ዕውቅና ተሰጠ።

በዕውቅና አሰጣጥ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ “ስርዓተ ምግብ ከዘላቂ የልማት ግቦች አንዱ አንኳር ጉዳይ በመሆኑ ተቋሞቻችሁን ለጡት ማጥባት ምቹ ያደረጋችሁትን እያመሰገንኩ ባለው ሀብት በትኩረት መስራት ይገባል” ብለዋል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ሕፃናት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር መሠረት ዘላለም በበኩላቸው ጡት ማጥባት በትንሽ ወጪ ብዙ ማትረፍ የሚያስችል ዘዴ በመሆኑ ለጡት ማጥባት የሚሰጠውን መልካም ባህል ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።

አያይዘውም ዕውቅና የተሰጣቸው ጤና ተቋማት በቁርጠኝነት እንዲቀጥሉና ለሌሎች ተቋማትም አርአያ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

ጡት ማጥባት በሀገሪቱ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ አስመልክቶ ገለፃ ያደረጉት በጤና ሚኒስቴር የስርዓተ ምግብ ኬዝ ቲም አስተባባሪ ወይዘሮ ሕይወት ድርሳኔ የጡት ወተት ለህፃናት ዘርፈብዙ ጠቀሜታ ስላለው በምንም አይነት ሁኔታ እስከ 6 ወር የጡት ወተት ብቻ መስጠት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በኮቪድ 19 የተያዘች እናት እንኳን ብትሆን ከጥንቃቄ ጋር ማጥባት እንዳለባትም ገልጸዋል።

በመድረኩ ዕውቅና የተሰጣቸው ጤና ተቋማት ተወካዮች ምርጥ ተሞክሮዎቻቸውን አጋርተዋል።

ዕውቅና ከተሰጣቸው 14 ተቋማት መካከል አምስቱ ከአፋር፣ አራቱ ከሶማሌ፣ ሶስቱ ከኦሮሚያ፣ አንድ ከአማራ እና አንድ ከደቡብ ክልል መሆናቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.