Fana: At a Speed of Life!

ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ የሚከተሉ ሰዎች ከበሽታ ነጻ የሆኑ ረጅም አመታትን ያሳልፋሉ – ጥናት

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ የሚከተሉ ሰዎች ከበሽታ ነጻ የሆኑ ረጅም አመታትን እንደሚያሳልፉ አንድ ጥናት አመላከተ።

በአሜሪካ ከ20 ዓመታት በላይ በተካሄደው ጥናት 111 ሺህ ሰዎች ላይ የጤና ክትትል ተደርጓል።

በተደረገው ጥናት የተሳተፉ ሰዎች ከሲጋራ እና የአልኮል መጠጥ ሱስ ነጻ የሆኑ፣ ጤናማ አመጋገብ ስርአት የሚከተሉ፣ በቀን ቢያንስ ለግማሽ ሰዓት ያክል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ እና የተስተካከለ የሰውነት አቋም ያላቸው ናቸው።

በተደረገው ክትትልም በዚህ ሂደት ያለፉ ሰዎች ረጅም አመታትን ከበሽታ ነጻ ሆነው ያሳልፋሉ ነው የተባለው።

በዚህም ሴቶች ከካንሰር፣ ከልብና ተያያዥ ችግሮች፣ ከአይነት ሁለት የስኳር በሽታ እና የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ፥ ነጻ የሆኑ 10 አመታትን ጤናማ የህይዎት ዘይቤ ከማይከተሉት ይልቅ ያሳልፋሉ ተብሏል።

በአጠቃላይ ደግሞ በህይዎት ዘመናቸው 34 አመታትን ከእነዚህ በሽታዎች ነጻ ሆነው እንደሚያሳልፉም ጥናቱ አመላክቷል።

ወንዶች ደግሞ ጤናማ የህይዎት ዘይቤ ከማይከተሉት ይልቅ ከተጠቀሱት በሽታዎች ነጻ የሆኑ ሰባት አመታትን ያሳልፋሉም ነው ያሉት፤ በህይዎት ዘመናቸው ደግሞ 31 አመታትን ከእነዚህ በሽታዎች ነጻ ሆነው እንደሚያሳልፉም በጥናቱ ተጠቅሷል።

ጥናቱ ከላይ የተጠቀሱትን ጤናማ የአኗኗር ዘይቤዎች የሚከተሉ ሰዎች ረጅም እድሜ መኖር ብቻ ሳይሆን በእነዚህ በሽታዎች ቢጠቁ የመዳን እድላቸው ከፍተኛ መሆኑም ተነስቷል።

በቀን በርከት ያለ ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች እና ለከፍተኛ ውፍረት የተጋለጡ ሰዎች ደግሞ በአንጻሩ ለእነዚህ በሽታዎች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑም ተጠቅሷል።

ምንጭ፡-ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.