Fana: At a Speed of Life!

ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ ለሚከሰት የእይታ ችግር ይዳርጋል – ጥናት

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 23 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ በተለይም ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ ለሚከሰት የእይታ ችግር ሊዳርግ እንደሚችል አንድ ጥናት አመላከተ።

ለሁለት አስርት አመታት የተደረገውና ከሰሞኑ ይፋ የሆነው ጥናት አመጋገብ ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ ለሚከሰት የእይታ ችግር መንስኤ እንደሚሆን ያመላክታል።

በብሪታንያ የተደረገው ጥናት ሰዎች አመጋገብ ከዓይን ጤንነት ጋር እንደሚገናኝ ግንዛቤው እንደሌላቸው ይገልጻል።

ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ በተለይም እድሜያቸው በገፋ ሰዎች ላይ ከእድሜ ጋር ተያይዞ ለሚመጣ የእይታ ችግር እንደሚያጋልጥም ነው ተመራማሪዎቹ የተናገሩት።

እንደ ተመራማሪዎቹ ገለጻ ቀይ ስጋ፣ እንቁላል፣ ጣፋጭ ምግቦችና ስኳር የበዛባቸው መጠጦች፣ የተቀነባበሩና በዘይት ተጠብሰው የሚዘጋጁ ምግቦች፣ የቅባት ይዘታቸው ከፍ ያሉ የወተት ተዋጽኦዎች እና በበዛ መጠን የተቀነባበሩ የጥራጥሬ ውጤቶች ለዚህ ችግር የማጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው።

ብርሃንን ተቀብሎ ምስልን ወደ አዕምሮ የሚልከው የአይን ክፍልን የሚጎዳና እይታን የሚያደበዝዝ ችግር መፍጠርም የዚህ ውጤት ነው ብለዋል።

ተመራማሪዎቹ በዚህ ችግር የሚጠቁ ሰዎች ችግሩ ከመከሰቱ ቀደም ብሎ ምንም አይነት ምልክት እንደማያዩ ጠቅሰው ይህም አደገኛ መሆኑን ነው የገለጹት።

ችግሩ ቀድሞ ምልክት አለማሳየቱ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ከባድ እንደሚያደርገውም ይጠቅሳሉ።

ለዚህም የእይታ ችግር ሊፈጥሩ ከሚችሉ ምግቦች በመራቅ በሽታውን ከጅምሩ መከላከል እንችላለን ይላሉ ተመራማሪዎቹ።

ይፋ ባደረጉት ጥናታቸውም አመጋገቡ ለችግሩ መንስኤ ሊሆን ይችላል ነው ያሉት።

ከላይ የተጠቀሰውን አመጋገብ የሚከተሉ ሰዎች ከማይከተሉት በሶስት እጥፍ በበለጠ ለዚህ ችግር ተጋላጭ ይሆናሉም ብለዋል በማብራሪያቸው።

ምንጭ፡-medical news today

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.