Fana: At a Speed of Life!

ፈዋሽነቱ 95 በመቶ ይደርሳል የተባለ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሞዴርና የተባለው ኩባንያ የሞከረው የኮሮና ቫይረስ ክትባት 94 ነጥብ 5 በመቶ ፈዋሽ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ሞዴርና ይፋ ያደረገው ይህ ክትባት በአሜሪካ ሁለተኛውና ትልቅ ግኝት ተብሎለታል፡፡

የአሜሪካ የተላላፊ በሽታዎች ተቋም ኃላፊ አንቶኒዮ ፉቺ ግኝቱን አስመለክተው ይህ ትልቅ ዜና ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ሞዴርና ክትባቱን በስራ ላይ እንዲውል በቀጣዩ ሳምንት እንደሚያመለክትም ነው የገለጸው፡፡

በሙከራው ወቅት 30 ሺህ አሜሪካውያን መሳተፋቸውን ነው የተነገረው፡፡

በተጨማሪም በመጪዎቹ ሳምንታት 2 ሚሊየን መጠን ያለው ክትባት እንደሚያመርት ገልጾ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ደግሞ 1 ቢሊየን መጠን ያለው ክትባት በዓለም ዙሪያ ለማሰራጨት ዕቅድ መያዙን ይፋ አድርጓል፡፡

ከሳምንት በፊት የአሜሪካው ፋይዘር እና የጀርመኑ ባዮንቴክ ፈዋሽነቱ 90 በመቶ የተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡

የሁለቱ ኩባንያዎች ክትባት የተለዩ ማቀዝቀዣዎችን ይፈልጋል የተባለ ሲሆን የሞዴርና በአንጻሩ በኔጌቲቭ 20 ዲግሪ ሴሊሺየስ ውስጥ ለስድስት ወራት እንዲሁም በመደበኛ ማቀዝቀዣ ውስጥ ደግሞ ለአንድ ወር ይቆያል ተብሏል፡፡

ከነዚህ ከሁለቱ ክትባቶች በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ሩስያ 92 በመቶ ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ ክትባት ይፋ አድርጋለች፡፡

 

ምንጭ፡-ቢቢሲ

በአብርሃም ፈቀደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.