Fana: At a Speed of Life!

መገናኛ ብዙሃን የንግግር ባህል መዳበር ላይ እና ብዝሃነትን የሚቀበል ዜጋ መፍጠር ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 25ኛ ዓመቱን አስመልክቶ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

በፓናል ውይይቱ “ፋና ከየት ወዴት” እንዲሁም ”የሚዲያ ሚና በሃገረ ብሄርና ሀገረ መንግስት ግንባታ” በሚሉ ርዕሶች ሁለት ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሚዲያ ተቋማት ሃላፊዎች፣ ወጣቶች፣ የሙያ ማህበራት ተወካዮችና ሌሎችም በፓናል ውይይቱ እየተሳተፉ ነው።

በዚህ የፓናል ውይይትም ላይ መገናኛ ብዙሃን የንግግር ባህል መዳበር ላይ እና ብዝሃነትን የሚቀበል ዜጋ መፍጠር ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው ተገልጿል።

መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ለሀገረ ብሄር ግንባታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ለማበርከትአካሄዳቸውን ቆም ብለው መመልከት ይኖርባቸዋልም ተብሏል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠንነትና ኮሙዩኒኬሽን ጽምህርት ቤት መምህር የሆኑት ዶክተር ዮሀንስ ሽፈራው ናቸው።

የመገናኛ ብዙሃን እውነትን፣ገልልተኝነትንና አለማዳላትን በተግባር ዋነኛ መርሆቻቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን የንግግር ባህል መዳበር ላይ እና ብዝሃነትን የሚቀበል ዜጋ መፍጠር ላይ ማተኮር እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

አርቆ አለማየት የሀገር ግንባታ ጠር ነው ያሉት ጥናት አቅራቢው መገናኛ ብሁሃን ታሪክ ብቻ ከመተንተን ሀገሪቱ የት ነች? የትስ ትደርሳለች በሚለው ላይ ማተኮር አለባቸውም ነው ያሉት።

መገናኛ ብዙሃን በስራዎቻቸውም እኛና እነርሱ የሚለውን ፈራጅ አገላለጽ ማስወገድ ይጠበቅባቸዋልም ተብሏል።

የኢፌዴሪ የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ንጉሱ ጥላሁን÷ 25ኛ አመቱን እያከበረ ያለው ፋና በሃገሪቱ የሚዲያ ታሪክ የእድገትና ለውጥ ማሳያ ሆኖ መቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።

የፋናን የ25 አመታት ጉዞ ማየት የኢትዮጵያን የ25 አመት የሚዲያ ድክመትና ጥንካሬ ጉዞን እንደማየት እንደሚቆጠርም ገልጸዋል።

አቶ ንጉሱ አያይዘውም ፋና አማራጭ በሌለበት ወቅት አማራጭ ሆኖ በመቅረብና ተመራጭና ተወዳዳሪ ሆኖ ለ25 አመታት መዝለቁን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው÷ ተቋሙ በሃገረ መንግስት ግንባታው የበለጠ ተሳትፎውን በማጠናከር ለልማትና ለህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መስራት እንደሚጠበቅበት አንስተዋል።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው ፋና ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር እዚህ መድረሱን አስረድተዋል።

ፋና የሃሳብ ነጻነትን፣ ሞጋችነትንና አዲስ አስተሳሰብን እየፈጠረ መምጣቱን ጠቅሰው ይህን ሂደት አጠናክሮ ለማስቀጠል ቃል ይገባልም ብለዋል።

በአላዛር ታደለ እናተስፋዬ ከበደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.