Fana: At a Speed of Life!

ፋና 100 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ በደሴ ያስገነባው የሚዲያ ኮምፕሌክስ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 100 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ በደሴ ከተማ ያስገነባው የሚዲያ ኮምፕሌክስ ተመረቀ።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው፥ ሚዲያ የመረጃ ተደራሽ ብቻ ሳይሆን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የአካልም የሃብትም ተደራሽ የመሆን ትልሙን እውን እያደረገበት ነው ብለዋል፡፡

ግንባታው ሁሉንም አገልግሎቶች አካታች እንዲሆን ታስቦ መሆኑን ገልጸው፥ በሬዲዮ ሲሰሩ የነበሩትን ስራዎች ምቹና ተደራሽነት ማሳደግን እንዲሁም የቴሌቪዥንና የዲጂታል ሚዲያውን ማዕከል ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተደራሽነት ሀገርን የሚያስተሳስር መሆኑ ከማዕከል ብቻ ሳይሆን ከክልል ወደ ማዕከል የሚሰራጩ ጉዳዮች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ በሚዲያ ዘርፍ ማህበረሰብ ተኮር ጉዳዮችን በማስተናገድና በማሳተፍ በሀገራችን የሚዲያ ኢንዱስትሪ ተወዳጅና ተመራጭ ሊሆን የቻለ የብዙሃን ድምጽ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ከሁሉ በላይ የይዘት፣ ብዘሃነትና ጥራት ከትርፋማነት በላይ የሚል መርህ ያነገበው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፥ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የሬዲዮ ስርጭት አድማስ በማስፋት በማዕከል ደረጃ ከሚሰራጨውና ከተወዳጁ ፋና 98 ነጥብ 1 በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ አስር የክልል ኤፍ ኤም ጣቢያዎችንና ተወዳጅ የቴሌቪዥን ጣቢያ አለው ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው፡፡

ዘመኑ በሚዋጀው የዲጂታል ሚዲያ ዘርፍም ማህበረሰብን በማገልገል ረገድ በኢትዮጵያ ተመራጭና ተወዳጅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስራ ላይ ካሉት አስር የክልል ኤፍ ኤም ጣቢያዎች ውስጥ የደሴ ፋና 96 ነጥብ 0 በአማራ ክልል መንግስት ከተቋቋሙ ሦስት የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አቶ አድማሱ አክለውም ፥ የደሴ ፋና 96 ነጥብ 0 ከተመሰረተና ስርጭቱ በሚደርስባቸው በአማራ ክልለ መንግስት በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ሰሜን ወሎና ደቡብ ወሎ ዞኖችና እንዲሁም በአፋር ክልል አካባቢዎች የመረጃ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ 12ኛ ዓመት እያስቆጠረ ነው ብለዋል፡፡

ዛሬ የሚመረቀው ዘመናዊ ህንጻ ሀገራችን በተለይም የጣቢያችን ቀጥተኛ አድማጭ ደምበኛና እንደባለቤትም ሲጠቀምበት የቆየውን ደጉ ህዝባችንና በየደረጃው ያለው አመራር በወራሪው ቡድን የደረሰበትን ከፍተኛ ችግር ተቋቁሞ በርካታ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ስራዎች በሚሰራበት ማግስት በመሆኑ ትርጉሙን ለየት ያድርገዋል ብለዋል፡፡

100 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ የተገነባው ዘመናዊ ህንጻ በርካታ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ባለ ስምንት ወለል ከምድር በታች ደግሞ ሦስት ተጨማሪ ወለሎችን ያካተተ ነው ብለዋል፡፡

የሚዲያ ኮምፕሌክሱ፥ ወቅቱን የሚጠይቀውን ስቱዲዮ የያዘና የቴሌቪዥን ስቱዲዮ ታሳቢ ያደረገ ጠቁመዋል።

ይህን ዘመናዊ ህንጻ ፋና ይገንባው እንጂ ዘላቂ ሃብትነቱ የህዝቡ ነው ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.