Fana: At a Speed of Life!

ፌስቡክና ትዊተር ከኮሮናቫይረስ የተሳሳተ መረጃ ጋር በተያያዘ በፕሬዚዳንት ትራምፕ ገጽ ላይ እርምጃ ወሰዱ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ የሆኑት ፌስቡክና ትዊተር የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የተሳሳተ መረጃ አሰራጭተዋል በሚል በገፃቸው ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን አስታወቁ።

የማህበራዊ ትስስር ድረ ገፆቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የህፃናት የበሽታ መከላከል አቅም ከፍተኛ በመሆኑ ለኮሮና ቫይረስ አይጋለጡም በሚል መረጃ በማሰራጨታቸው ነው እርምጃውን የወሰዱት።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከፎክስ ቴሌቪዥን ጋር በስልክ ባደረጉት ቆይታ ላይ በመላው ሀገሪቱ ትምህርት ቤቶች መልሰው መከፈት እንዳለባቸው እና ለዚህም ምክንያታቸው ህፃናት ለቫይረሱ ተጋላጭ ባለመሆናቸው ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ይህንን ተከትሎም ፌስቡክ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከፎክስ ዜና ጋር ያደረጉትን የድምጽ ቅጂ ቪዲዮ “ከኮሮና ጋር በተያያዘ አደገኛ እና የተሳሳተ መረጃ” በሚል የፕሬዚዳንቱን መልእክት ከገፁ ማንሳቱን አስታውቋል።

የፌስቡክ ኩባንያ ቃል አቀባይ በትናንትናው እለት እንዳስታወቀው፥ በፕሬዚዳንት ትራምፕ ገጽ ላይ የተለቀቀው ቪዲዮ ከበሽታ መከላከል ጋር በተያያዘ ሀሰተኛ መረጃ በመያዙ እና የኩባንያውን ፖሊሲ የሚጥስ በመሆኑ ከገፁ መነሳቱን አስታውቋል።

ፌስቡክ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገፅ ላይ የተጫነ መረጃ ላይ እርምጃ ሲወስድ እና ከገፃቸው ላይ ሲያነሳም ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

ሌላኛው የማህበራዊ ትስስር ገፅ የሆነው ትዊተርም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከኮሮና ጋር በተያያዘ የለቀቁትን የተሳሳተ ይዘት ያለውን ቪዲዮ እስኪያነሱት ድረስ ገፃቸውን ማገዱን አስታውቋል።

ትዊተር ያገደው ገፅ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለምርጫ ቅስቀሳ የሚጠቀሙበት “@TeamTrump” የተባለውን ይፋዊ የትዊተር ገፅ መሆኑንም አስታውቋል።

የትዊተር ቃል አቀባይ እንዳስታወቁት በገጹ ላይ የተጫነው ቪዲዮ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የኩባንያውን ፖሊሲ የሚጥስ ሆኖ ተገኝቷል።

ገፁን የሚያስተዳድረው አካልም ገፁ ከእግድ እንዲለቀቅ ሌላ ይዘት ትዊት ከማድረጉ በፊት ቪዲዮውን ማንሳት እንደሚጠበቅበትም ነው ቃል አቀባዩ ያስታወቁት።

ትዊተር ባሳለፍነው ወርም ከኮሮና ቫይረስ እና ከሀይድሮክሲክሎሮኪን መድሃኒት ጋር በተያያዘ የተሳሳተ መረጃ አሰራጭቷል በሚል የዶናልድ ትራምፕ ልጅ ገጽን በጊዜያዊነት ዘግቶት እንደነበረም ይታወሳል።

 

ምንጭ፦ bbc.com

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.