Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህና ሌተናል ጄኔራል አዲስ ተድላ ከጣሊያን ኤምባሲ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህና ሌተናል ጄኔራል አዲስ ተድላ ከጣሊያን ኤምባሲ እንዲለቀቁ ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ትዕዛዝ ሰጠ።

በእነ ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም መዝገብ የተከሰሱት የቀድሞ ፍርደኞች ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህና ሌተናል ጄኔራል አዲስ ተድላ ላይ የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዘርፍ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት አስተዳደር የአመክሮ አቤቱታ ከአስተያየት ጋር አቅርቧል።

በዚሁ መሰረት አቤቱታውን የመረመረው ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል።

በጣሊያን ኤምባሲ ላለፉት 30 ዓመታት ተጠልለው የሚገኙት ሁለቱ ተከሳሾች ካሉበት የተከለለ ውስን ስፍራ ሊላቀቁ ይገባል ሲል ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን መርምሮ በአብላጫ ድምጽ ብይን ሰጥቷል።

በዚሁ መሰረት “ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህና ሌተናል ጄኔራል አዲስ ተድላ ከጣሊያን ኤምባሲ እንዲለቀቁ” ሲል ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ትዕዛዙ በቀጥታ ለጣሊያን ኤምባሲ ሳይሆን በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለጣሊያን ኤምባሲ እንዲሁም ለቀድሞ ፍርደኞች ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህና ሌተናል ጄኔራል አዲስ ተድላ እንዲደርስ ይደረግ ዘንድ አዟል።

ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህና ሌተናል ጄኔራል አዲስ ተድላ የቀድሞ ፍርደኞች አሁን ግን በአመክሮ በፍርድ ቤት የተለቀቁ መሆኑን አውቀው መብታቸውን ለማስከበር ጥበቃም ሆነ ክትትል እንዲያደርጉ ለሚመለከተው አካል እንዲጻፍ ፍርድ ቤቱ አዟል።

በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ላይ በተራ ቁጥር ሁለት የተሰየሙት ዳኛ ተከሳሾቹ በኤምባሲ በስደተኛነት ተጠልለው ነበር እንጂ ፍርድ አግኝተው ቅጣታቸውን በማረሚያ ቤት ያልተቀበሉ በመሆናቸው ከመደበኛው የአመክሮ ስርዓት ውጭ የአመክሮ ጊዜያቸው እንደደረሰ በመቁጠር እንዲለቀቁ ከውሳኔ መደረሱ ላይ በልዩነት ወጥተዋል።

ላለፉት 30 ዓመታት አዲስ አበባ በሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ ተጠልለው በቁም እስር ላይ የቆዩት ሁለቱ ከፍተኛ የደርግ

በኤምባሲው ተጠልለው የሚገኙት የ85 ዓመቱ ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህና የ77 አመቱ ሌተናል ጄኔራል አዲስ ተድላ ናቸው።

ሌተናል ኮሎኔል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያገለገሉ ሲሆን የ77 ሌተናል ጄኔራል አዲስ ተድላ ደግሞ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሆነው ያገለገሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ነበሩ።

እነዚህ ሁለት ከፍተኛ የቀድሞ ሹማምንት ከጣሊያን ኤምባሲ የቁም እስር እንዲወጡ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ በርካታ አካላት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ኢዜአ ዘግቧል።

ላለፉት 30 አመታት አዲስ አበባ በሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ ተጠልለው በነበሩት የደርግ ባለስልጣናት ላይ ተላልፎ የነበረው የሞት ፍርድ ወደ እድሜ ልክ እስራት ማሻሻያ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በፊርማቸው ማጽደቃቸው ይታወሳል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.