Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ የአቶ ልደቱን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለምርመራ ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዷል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አቶ ልደቱ አያሌው በቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ለአራተኛ ጊዜ ቀርበው ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ሲሆን መርማሪ ፖሊስም  ለምርመራ ተጨማሪ ሰባት ቀናት ተፈቅዶለታል።

አቶ ልደቱ አያሌው በተጠረጠሩበት በቢሾፍቱ ከተማ ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓመተ ምህረት የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ አመፅና ሁከት እንዲነሳ ወጣቶችን በማስተባበርና በገንዘብ በመርዳት ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ ሲደረግባቸው መቆየቱ ይታወቃል።

መርማሪ ፖሊስ በዛሬው እለት እጃቸው ላይ የተገኘ የሽግግር መንግስት መመስረቻ ሰነዶች፣ የስልክ ልውውጥ እና ሲዲ ለምርመራ መላኩን ገልፆ አጠቃላይ የምስክር ቃል ለመቀበል እና የእነዚህ የምርመራ ውጤት ለማምጣት 14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ብሏል።

አቶ ለደቱ አያሌው በበኩላቸው በጠበቃ ተወክለው “ከዚህ በፊት አምስት ጊዜ ታስሬ ማስረጃ ስለሌለ ፍርድ ቤት ነፃ ያድርገኝ፣ ለፍርድ ቤቱ ከፍ ያለ ክብር አለኝ፣ ነገር ግን አሁን ከሳሽ ብቻ ነው በተደጋጋሚ ጊዜ እየተሰጠው ያለው፣ ይህ ተገቢነት የለውም፣ እኔ የህክምና ማስረጃ አምጥቼ ለህክምና ዋስትና ስጠይቅ ውድቅ መደረጉ የአንድ ወገን ብቻ እየተሰማ መሆኑን ያሳያል፣ አራት ጊዜ ዳኞች እየተቀያየራችሁ ነው፣ መርማሪ ፖሊስ ተደጋጋሚ አንድ ዓይነት ምርመራ ነው እያቀረበ ያለው” የሚል መቃወሚያ አንስተዋል።

የወረዳው ፍርድ ቤትም ችሎቱ የጊዜ ቀጠሮ ነው፣ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ጉዳይ ደግሞ በተረኛ ዳኛ የሚታይ እንጂ ሌላ ጉዳይ የለም፣ ፍርድ ቤቱ ገለልተኛና ሚዛናዊ ሆኖ ነው የሚመለከተው፣ በሚቀርበው የምርመራ ውጤት ልክ መዝኖ ነው ጊዜ የሚሰጠው፣ ይህ የፖለቲካ ጉዳይ የሚታይበት ቦታ አይደለም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ከመርማሪ ፖሊስ ጋር አብሮ የተገኘው የከተማዋ ዐቃቤ ህግም “ህክምናውን በሀገር ውስጥ ማግኘት ይችላሉ ወደውጭ ቢወጡ በዚያው ሊቀሩ ይችላሉ” ሲል የዋስትና ጥያቄው ላይ መቃወሚያ አቅርቧል።

ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱም የአቶ ልደቱ አያሌውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ መርማሪ ፖሊስ ቀረኝ ያለውን የምርመራ ውጤት አጠናቆ እና አካቶ እንዲቀርብ ተጨማሪ የሰባት ቀናት ጊዜ ሰጥቷል።

 

 

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.