Fana: At a Speed of Life!

ፍትሃዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ፓርቲዎች ህግን መሰረት ያደረገ እንቅሰቃሴ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፍትሃዊ፣ ተኣማኒ፣ ነጻ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ በቅድመ ምርጫ ወቅት ፓርቲዎች ህግን መሰረት ያደረገ እንቅሰቃሴ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገለጸ።

ከፋና ብሮድካስቲነግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ፥ ቦርዱ የቅድመ ምርጫ ተግባራትን በሚፈለገው ደረጃ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ መሰረትም ጊዜያዊ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ይፋ ማድረግ፣ ግብዓት ማሰባሰብና የምርጫ ጣቢያዎችን በዘመናዊ መንገድ የማደራጀት ተግባር እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

የህግ ባለሙያው አቶ ብርሃኑ ታዬ በበኩላቸው፥ በቅድመ ምርጫ ወቅት ምርጫ ቦርድ ከሚያደርገው ዝግጅት በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጅት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በድጋፍ ማሰባሰብ እና የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የተዛቡ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግርን ከማሰራጨት መቆጠብ ያለባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም ሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር እንዲኖር ከማድረግ ባለፈ ምርጫን ተከትሎ የሚፈጠሩ ችግሮችን ማስቀረት ያስቻላል ነው ያሉት።

የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ዳንኤል አሰፋ፥ መራጮች በትምህርት ያገኙትን የህግና የፖለቲካ ንቃተ ህሊና በፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲና ፕሮግራም ላይ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

በምርጫ ሂደት የሚያጋጥሙ ክስተቶች በቦርዱ ብቻ ሊሸፈኑ እንደማይችሉ የገለጹት የቦርዱ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ፥ ፓርቲዎች የሚያከናውኑት እንቅስቃሴ ሃላፊነት የተሞላበት መሆኑ እንደሚገባው ጠቁመዋል።

ከዚህ ባለፈም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግስት፣ የፀጥታ አካላትና ህዝቡ በቅድመ ምርጫ ወቅት የሚስተዋሉ ችግሮችን በቅንጅት በመፍታት ረገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በበላይ ተስፋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.