Fana: At a Speed of Life!

ፍትሓዊ የሀብት ክፍፍልን ማስፈንና የዋጋ ግሽበትን በነጠላ አሃዝ ለማቆየት ታቅዷል- አቶ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያን ማዕከል በማድረግ ፍትሓዊ የሀብት ክፍፍል ማስፈንና የዋጋ ግሽበትን በነጠላ አኅዝ ለማቆየት መታቀዱን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ገለጹ።

ዘላቂ የልማት ፋይናንስ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ላይ ውይይት ተደርጓል።
ሚኒስትሩ ውጥኑን ባቀረቡበት ወቅት በኢትዮጵያ አሁንም በርካታ ዜጎች ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ ብለዋል።

የዕቅዱ ዓላማ በዋናነት የዜጎችን ሕይወት ማሻሻልና ብዙሃኑን የሚጠቅም አገራዊ ልማት ማረጋገጥ ነውም ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ዕቅዱ በዋናነት ባለፈው ዓመት የተጀመረውን የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕከል ያደረገ ነው።

ይህ ደግሞ የታክስ አሰባሰብ አቅምን ማሳደግ፣ የአገር ውስጥ ገቢ በስፋት መሰብሰብና የውጪ ኃብት ማግኘት አቅምን በማሳደግ ይታገዛል ይላሉ።

የልማት ድርጅቶች አፈጻጸም ማሻሻል፣ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠርና የውጭ ምንዛሪን ማሳደግም በስፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

”የተረጋጋ ዋጋ ማስፈን፣ ጠንካራ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር መተግበር፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውጤታማነት ማሻሻልና የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር ማጎልበት ከውጥኖቹ መካከል ናቸው” ብለዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥው ዶክተር ይናገር ደሴ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት የፋይናንስ ዘርፍ ተደራሽነት ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል ይላሉ።

ከተደራሽነቱ ጎንም ቁጠባን ማሳደግ፣ የውጪ ንግድ ሥርዓቱን ማሻሻልና ግሽበትን የመቆጣጠር ሥራው እንደሚጠናከር ገልጸዋል።

ዘርፉ ካለው የሕዝብ ብዛትና ሌሎች አገች ከደረሱበት አንጻር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተው፤ የሞባይል ባንኪንግን ጨምሮ የባንክ ደብተር ያለው ሰው እጅግ ውስን ነው ብለዋል።

”የአገሪቷን የዕዳ ጫና የመቀነስ ሥራም በትኩረት ይሰራል” ያሉት ገዢው፡ የካፒታል ገበያን ጨምሮ አማራጭ የፋይናንስ አሰራሮች እንደሚተገበሩ አስታውቀዋል።

በዕቅዱ ላይ አስትያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖና የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደርቤ አስፋው የግብርና ፋይናንስ ልዩ ትኩረት ይሰጠው ይላሉ።

ግብርና እንድ አገር ፈታኝ ለሆኑት ጉዳዮች ሁሉ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰው፤ ለአብነትም ግብርና የውጭ ምንዛሪ አይጠይቅም፣ የምግብ ዋስትናን ያረጋገጣል ብለዋል።

በዕቅዱ ላይ በየዘርፉ የሚደረገው ውይይት እንደቀጠለ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.