Fana: At a Speed of Life!

ፓርቲዎች በመጪው ምርጫ አማራጭ ሀሳቦቻቸውን በሰከነ መንገድ ለህዝቡ ማቅረብ እንዳለባቸው ምሁራን አሳሰቡ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ፓርቲዎች በመጪው ምርጫ ያፎካክረናል ያሉትን ስትራቴጂ፣ አማራጭ ሀሳብ በሰከነና በበሰለ መንገድ የምርጫ ሰላማዊ አውድን ጠብቀው እንዲያስተላልፉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን አሳሰቡ፡፡

ፓርቲዎች በመጪው ምርጫ ያሏቸውን የመመረጫ ሀሳብ አደራጀተው የሚያስተዋውቁበት ወቅት እንደመሆኑ ለመነቃቀፍ፤ ወደ ግጭት ከሚወስዱ ትችቶች መራቅ እንደሚጠበቅባቸው የፖምሁራኑ ገልጸዋል፡፡

ምሁራኑ ስነ ምግባር በማይጠብቁት ላይም የፍትህ ተቋማት ፈጣን እርምት ለመውሰድ ሊዘጋጁ ይገባል ነው ያሉት።

የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶክተር ደጉ አስረስ   በቀጣዩ ምርጫ ገዢው ፓርቲን ጨምሮ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀዳሚ ተግባራቸውን የሚጀምሩት ሰላማዊ ከሆነ የምርጫ ስነ ምግባር መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

በቅድመ ምርጫ ከግጭት ቀስቃሽ ንግግሮችና ቅስቀሳዎች በመውጣት ሰላማዊ ሂደትን በማያውኩ እንቅስቃሴዎች ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።

ይህንንም በሀሳብ ብልጫ በምርጫ የማሸነፍ መንገድን ብቻ ግብ የማድረግ ሂደት ነመሆኑን ነው የገለጹት።

እንዲሁም የምርጫ ስነ ምግባር ደንብን ተከትለው ለመራጮች አማራጮቻቸውን ማሳወቅ ስራ ላይ ማተኮር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የሌሎች ሀገራትን የቅድመ ምርጫ አለመረጋጋቶችን ማሳያ የሚያደርጉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ለግጭት የሚዳርጉ የቅድመ ምርጫ ስራዎች ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳላቸው አንስተዋል።

በተለይም በሀገራቱ የውስጥ አለመረጋጋት ገፊ ምክንያት የሚሆኑ አጀንዳዎችን በማንሳት የመወዳደሪያ ካርታ መምዘዛቸው ተጽእኖ ሲፈጥር እንደሚስተዋል ታዝበዋል።

በኢትዮጵያም ቀጣዩ ምርጫ ነባራዊውን የሀገሪቱን የውስጥ ችግሮች መጠቀሚያ ከማድረግ እንቅስቃሴ መቆጠብ አለባቸው ብለዋል።

ሌላኛው መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ባምላክ ይደግ በበኩላቸው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በፓርቲዎች የምርጫ ስነ ምግባር ላይ ጥብቅ ሆኖ መከታተል ይኖርበታል ነው ያሉት።

ምሁሩ ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን መስፈርት ያላሟሉ ፓርቲዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን እንደ አስረጂነት አንስተዋል።

ፓርቲዎቹ ለተቋማት ተገዢ የመሆን ስነ ምግባርን ሊላበሱ ይገባልም ብለዋል።

በቅድመ ምርጫ በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችንም በመከታተል፤ አፍጣኝ የእርምት እርምጃ መውሰድ ይገባል የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራኑ ፓርቲዎች በስነ ምግባር የጸና የምርጫ ሂደት ላይ ከወዲሁ ልምምድ በማድረግ በምርጫ ወቅትም ሆነ በድህረ ምርጫ በሚኖሩ ችግሮችን መፍታት ይቻላል ብለዋል።

በመጨረሻም  የስነ ምግባር ችግር ከመስተዋሉ አስቀድሞ አሁን ላይ የዘርፉ ባለድርሻዎች ምህዳሩን ተሳታፊዎች የማንቃትና የማብቃት ስራ ከወዲው እንዲሰሩ መክረዋል።

በሀይለኢየሱስ መኮነን

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.