Fana: At a Speed of Life!

ፓስፖርትን ጨምሮ ሀሰተኛ ሰነድ ሲያዘጋጅ የነበረው ግለሰብ ተያዘ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በመኖሪያ ቤት ውስጥ ፓስፖርትን ጨምሮ የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጅ የነበረው ግለሰብ ተያዘ፡፡
 
ግለሰቡ በህብረተሰቡ ጥቆማ ተይዞ ምርመራው እየተጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
 
ተጠርጣሪው የተያዘው አሜሪካን ግቢ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው ተብሏል፡፡
 
ፖሊስ ኮሚሽኑ ባካሄደው ፍተሻ የግለሰቡ መኖሪያ ቤት ውስጥ በሀሰት የተዘጋጁ ፓስፖርቶች፣ ማህተሞች፣ ቲተሮች፣ የተለያዩ የትምህርት ማስረጃዎች እና የዝሆን ጥርስ መያዙን ጉዳዩን የያዙት መርማሪ ዋና ሳጅን አብድልካሪም አህመዲን ተናግረዋል፡፡
 
የመርካቶ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል መከላከል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር እዮብ ተከተል አካባቢው በመልሶ ማልማት ላይ የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ህገ-ወጥ ተግባራት ሲፈፀሙ እንደሚስተዋል ገልጸዋል፡፡

 

የልማት ስራውን ለማከናወን ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ወደ ስራ በመግባት አካባቢውን ከህገ-ወጦች መከላከል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ምክትል ኢንስፔክተሩ በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል በአገርና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል አንስተዋል፡፡
በዚህ ድርጊት የሚሳተፉ አካላትን አጋልጦ በመስጠት ህብረተሰቡ ህገወጥነትን በመከላከል የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ምክትል ኢንስፔክተሩ ማሳሰባቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.