Fana: At a Speed of Life!

ፔፕሲኮ የተባለው ኩባንያ በዘይት ምርት እና በምግብ ማቀነባበሪያ ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው ፔፕሲኮ ኩባንያ በኢትዮጵያ በዘይት ምርት፣ በምግብ ማቀነባበሪያ እና የተለያዩ የፍራፍሬ ጭማቂ ምርቶችን በማምረት ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለፀ፡፡

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያም ከኩባንያው የአፍሪካ ቅርንጫፍ ከፍተኛ ማኔጅመንት አባላት ተወያይተዋል።

ሃላፊዎቹ ኢትዮጵያ ለኩባንያው ኢንቨስትመንትና ምርቶች ገበያ ስትራቴጂክ ሀገር ተደርጋ እንደምትወሰድ ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም ኩባንያው በዘይት ምርት፣ በምግብ ማቀነባበሪያ እና የተለያዩ የፍራፍሬ ጭማቂ ምርቶችን በማምረት በኢትዮጵያ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

ዶክተር ሽፈራው ኩባንያው በአፍሪካ አህጉር በተለይም በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ላይ ትኩረት አድርጎ መስራቱ ለአፍሪካም ሆነ ለኢትዮጵያ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት እንደሆነና ኩባንያው ላከናወናቸው መልካም ተግባራት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለእርሻ ምርት ማቀነባበሪያ ዘርፍ ግንባር ቀደም ትኩረት እንደምትሰጥ እና ፔፕሲኮ ኩባንያ ለሚያቅዳቸው ፕሮጀክቶች ሙሉ ድጋፍ እነደምታደርግም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን በቅርበት ለመረዳት፣ ከመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ምክክር ለማድረግ እንዲሁም ከግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ለማድረግ የኩባንያው ኃላፊዎች በኢትዮጵያ ጉብኝት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኩባንያ ኃላፊዎችም በቅርቡ ጉብኝት እንደሚያደርጉና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚወያዩ ቃል መግባታቸውን በደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው ፔፕሲኮ በተለያዩ ሀገራት በግብርና ምርት ማቀነባበር እና ለስላሳ መጠጦችን በማምረት ይታወቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.