Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ከታንጀብል ሆፕ ፋውንዴሽ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ከታንጀብል ሆፕ ፋውንዴሽን ድርጅት መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሊሊ ዮሴፍ ጋር ተወያዩ።

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የፋውንዴሽኑ ተግባር ለቆሙለት አላማ ቁርጠኛ ከመሆኑም በላይ ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቷ አያይዘውም ሴት ልጆችን ማስተማር ህይወታቸው እንዲቀየር የማድረጊያ መንገድ መሆኑን ጠቁመዋል።

በግል ተነሳሽነት የሚሰሩ ስራዎች ብዙ ውጤት ማስገኘታቸውን ጠቅሰው ከዚህ አንጻር ዜጎች እንዲነሳሱ ጥሪ ማቅረባቸውን ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የታንጀብል ሆፕ ፋውንዴሽን ድርጅት መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሊሊ ዮሴፍ በበኩላቸው፥ ፋውንዴሽኑ በኮፈሌ 100 እንዲሁም በሲዳማ አካባቢ ደግሞ 20 ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተናገድ የሚችሉ ትምህርት ቤቶች መገንባቱን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።

በድርጅቱ ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን እስከሚያጠናቅቁ ድረስ ድጋፍ የሚደረግላቸው ከመሆኑም ባሻገር ልጆች ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ በማሰብ ለቤተሰቦቻቸው የጥራጥሬና የምግብ ዘይት ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ነው የተናገሩት።

በፈረንጆቹ 2011 የተመሰረተው ታንጅብል ሆፕ ፋውንዴሽን በገጠር የሚኖሩ ልጃገረዶችን ከድህነት ማውጣትና አቅማቸውን ለማዳበር የሚሰራ ድርጅት ነው።

ድርጅቱ በኢትዮጵያ በምዕራብ አርሲ ዞን ኮፈሌ አካባቢ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.