Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከተመራው የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከተመራው የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያይተዋል ።

የልዑካን ቡድኑ መሪ ፔካ ሀቪስቶ ህብረቱ በትግራይ ያለውን የዕርዳታ እና የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዲሁም በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የመወያየት፣ ወደ ትግራይ በመሄድም ሁኔታዎችን የማየት እቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለመንግስታትም ሆነ ለዓለም አቀፍ ተቋማት እና መገናኛ ብዙሀን የትግራይን ሁኔታ እንዲመለከቱ ማድረጉን አስታውሰዋል።

እርዳታን በተመለከተም የኢትዮጵያ መንግስት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን እርዳታ በራሱ ሀይል እያዳረሰ መሆኑን ፕሬዘዳንቷ አስታውሰዋል።

በህግ ማስከበር እንቅስቃሴው ተከሰቱ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንም ለማጣራት እንቅስቃሴ መጀመሩንም አንስተዋል።

የልዑካን ቡድኑ ከ2 ወራት በፊት ለተመሳሳይ ዓላማ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ የልዑካን ቡድኑ መሪ ፔካ ሀቪስቶ እንዳሉት በትግራይ ነገሮች እየተሻሻሉ መጥተዋል።

ቡድኑ በኢትዮጵያ ቆይታው የተረዳውን እና የደረሰበትን ድምዳሜ በሚያዚያ ወር አጋማሽ ለህብረቱ የሚኒስትሮች ስብሰባ እንደሚያቀርብ ማስታወቁን ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.