Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይቱ ሁለቱን አገሮች ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል ነው የተባለው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ ከአቶ ደመቀ መኮንን ከጋር በነበራቸው ቆይታ በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ተብራርቶላቸዋል።
በአሁኑ ወቅት ክልሉን መልሶ የመገንባትና የሰብአዊ ድጋፍ ስራዎችም ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸውላቸዋል።
“በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ክልል ለሚደረጉ የሰብአዊ ድጋፎች መንገዶች ሁሉ ክፍት ናቸው” ያሉት አቶ ደመቀ 85 በመቶ በሚሆነው የክልሉ አካባቢዎች የምግብ እና የመድሃኒት አቅርቦት እየተዳረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ የተፈጠረው ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝም አቶ ደመቀ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን ስትራቴጂክ አጋር አገሮች እንደመሆናቸው መጠን ችግሩን በሰለጠነ እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ኢትዮጵያ ፅኑ ፍላጎት ያላት መሆኑንም አረገግጠውላቸዋል።
የህዳሴ ግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር በጋራ መግባባት ላይ ተመስርቶ እንዲካሄድና የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ኢትዮጵያ ጥረት ታደርጋለችም ነው ያሉት።
የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ ኢትዮጵያና እንግሊዝ የቆየና እስካሁንም የዘለቀ ጥልቅ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
እንግሊዝ በቀጣይም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሻ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀጠና ሰላምና መረገጋት እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ ለመደገፍም አገራቸው ፍላጎት እንዳላት ነው የገለጹት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መንግስት በትግራይ ክልል የሚያደርገውን የሰብአዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.