Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በህዳሴው ግድብ ላይ የሰጡት አስተያየት የሚወገዝና ተቀባይነት የሌለው ነው – ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በህዳሴው ግድብ ላይ የሰጡት አስተያየት የሚወገዝና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ ገለጹ፡፡

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ የፊታችን ሃሙስ የሚከበረውን 1 ሺህ 495ኛው የመውሊድ በዓል ምክንያት በማድረግ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሰጡትን አስተያየት አውግዘዋል፡፡

የፕሬዚዳንቱ አስተያየትም ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡

ተቀዳሚ ሙፍቱ ሃጂ ዑመር ነብዩ መሀመድ በምድር ቆይታቸው በጎ ነገሮችን ሰርተው ማለፋቸውንም ገልጸዋል፡፡

በበዓሉ ለሰላት ወደ መስጊድ የሄዱ ምዕመናን ባለመጨባበጥና ርቀትን በመጠበቅ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቁም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በመልዕክታቸው ኢትዮጵያውያን መተዛዘን፣ አብሮ መብላት እና መረዳዳት እንጅ መገዳደል ባህላቸው እንዳልሆነም አንስተዋል፡፡

ከዚህ አንጻርም አንዱ አንዱን መግደል ሊቆም፤ መጠፋፋት ሳይሆን ለሰላም በአንድነት መቆም ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ጠላትን ለመመከት አንድ መሆን ይገባል ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ለሃገሪቱ ልማት መስራት ይገባል ብለዋል በንግግራቸው፡፡

ለሀገር ሰላም የሚበጀው መጠፋፋት ሳይሆን መቀራረብና ይቅር መባባል መሆኑንም አስረድተዋል።

ማንም ሰው በህይወት እስካለ ድረስ የነብያችንን አደራ፣ አመራርና መልካም ፀባይ ሊከተል እንደሚገባውም አሳስበዋል።

በሀገሪቱ ላይ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከልና ሌሎችንም ፈተናዎች ለመሻገር የዜጎች አንድነት ወሣኝ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ሰው ከሀጥያት እስካልተቆጠበ ድረስ ወደፊት ከአንበጣ በተጨማሪ ሌላ መከራ ሊመጣ እንደሚችል ያስጠነቀቁት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር፥ የእምነቱን አስተምህሮ በመከተል ከሙስና፣ ከሌብነትና በደል ራስን ማራቅ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በፈቲያ አብደላ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.