Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሊቢያ እና ሶሪያ ቀውስ ዙሪያ ከቱርክ አቻቸው ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ጥር 19፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቱርክ አቻቸው ረሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ጋር በሊቢያ እና ሶሪያ ቀውስ ዙሪያ በስልክ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በሶሪያ የእርስ በርስ ግጭት ላይ የሚስተዋለውን አላስፈላጊ የውጭ ሃይል ጣልቃ ገብነት ማስቀረት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ መክረዋል።

በተጨማሪም የሊቢያ ተቀናቃኝ ሃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ በትኩረት መምከራቸውን የኋይት ሃውስ ቃል አቀባይ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

እንዲሁም በሶሪያ ኢድሊብ ግዛት በሀገሪቱ መንግስት እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መካከል እንደ አዲስ የተጀመረው ግጭት መቆም እንደሚገባው ስምምነት ላይ ደርሰዋል ነው የተባለው።

ግጭቱን ተከትሎ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሶሪያውያን መኖሪያ ቀያቸውን ለቀው በአቅራቢያ ወደ ሚገኘው የቱርክ ድንበር መሸሻቸው ተመላክቷል።

መሪዎቹ ለዓመታት የዘለቀው የሊቢያ እና ሶሪያ ቀውስ እልባት እንዲያገኝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

በሊቢያ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የትሪፓሊ መንግስት እና በጄኔራል ከሊፋ ሃፍታር የሚመራው አማጺ ቡድን ከፍተኛ ግጭት ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል።

በጄኔራል ሀፍታር የሚመራው አማጺ ቡድን ባሳለፍነው ዕሁድ ዕለት በሀገሪቱ መንግስት ሃይሎች ቁጥጥር ስር የምትገኘውን ሚስራታ ከተማ ለማስለቀቅ እንቅስቀሴ መጀመሩ ተገልጿል።

የሊቢያ ተቀናቃኝ ሀይሎች በቅርቡ በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ ያካሄዱት የተኩስ አቁም ደርድር ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል።

ምንጭ፦ ሬውተርስ እና አልጀዚራ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.