Fana: At a Speed of Life!

ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች በቅጣት እንዲያስመዘግቡ ሊደረግ ነው

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 19 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች በገንዘብ ቅጣት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ሊደረግ መሆኑን የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ከአዲስ አበባ ከአስሩም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ አመራሮች ጋር በሀብት ምዝገባ ዙሪያ ባደረገው ውይይት፥ በተቀመጠው መደበኛ የምዝገባ ጊዜ ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ የወረዳና የክፍለ ከተማ አመራሮች በገንዘብ ቅጣት በ5 ቀናት ውስጥ ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የጊዜ ገደብ ተቀምጧል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ እንደተናገሩት÷ ከአስሩ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈፃሚዎች መካከል በጊዜ ገደቡ ሀብታቸውን ያስመዘገቡት የቦሌ፣ የአራዳና የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ብቻ መሆናቸዉን ተናግረዋል።
ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች ከመስከረም 18 እስከ 22 ቀን 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በተሻሻለው የሃብት ማሳወቅ እና ምዝገባ አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 1/2013 መሠረት ለኮሚሽኑ የአንድ ሺህ ብር ቅጣት በመክፈል የሀብት ማስመዝገብ ግዴታቸውን እንዲወጡ የሚደረግ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሀብታቸውን በማስመዝገብ ግዴታቸውን የማይወጡትን ኮሚሽኑ በሙስና ወንጀል እንዲጠየቁ ጉዳዩን አግባብነት ላለው የምርመራ አካል የሚያስተላልፍ መሆኑን በኮሚሽኑ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መስፍን በላይነህ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ 30 የሚጠጉ የክፍለ ከተማ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን÷ በጉዳዩ ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ ተይዞ ሙስናን በጋራ መከላከል እንዲቻል የዚህ አይነት መድረኮች በቀጣይም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስተያየታቸውን መስጠታቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.