Fana: At a Speed of Life!

ሀዋሳና ቢሾፍቱን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች የድጋፍ ሰልፎች ተካሄዱ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሀዋሳና ቢሾፍቱን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ስራ በመደገፍ የተለያዩ የድጋፍ ሰልፎች ተካሂደዋል።

በሃዋሳ ከተማ ስታዲየም እየተካሄደ ባለው መርሃ ግብር ላይ በርካታ የከተማዋ እና የአካባቢው ነዋሪዎችን ጨምሮ በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ፣ የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ እና የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ሌዳሞ የድጋፍ ሰልፉ ላይ በመገኘት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች “ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድንና ብልፅግና ፓርቲን እንደግፋለን!፣ የብልፅግና ፓርቲ ለሀገራችን ህልውና እና ለህዝባችን ህይወት መሻሻል ያለውን ራዕይ እንደግፋለን!፣ ለውጡን ሊቀለብሱ የሚፈልጉ ኃይሎችን እንቃወማለን” የሚሉ እና ሌሎች ሌሎች መፈክሮችን ይዘው ድጋፋቸውን ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዎች የድጋፍ ሰፍል ተካሂዷል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ለብልፅግና ፓርቲ ያላቸውን ድጋፍ ገልፀዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ “ብልፅግና ለሁሉም፤ ሁሉም ለብልፅግና፣ ስድብ የኦሮሞ ባህል አይደለም፣ ከዶክተር ዐቢይ ጎን መሰለፍ የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ ነው፣ በፍቅር እንደመር በይቅርታ እንሻገር፣ አንድነት ለሰላምና ለብልፅግና” የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።

እንዲሁም የጉጂ ዞን ነጌሌ ከተማ እና የአካባቢው ነዋሪዎች በዛሬው እለት ባካሄዱት ሰልፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ለብልፅግና ፓርቲ ያላቸውን ድጋፍ ገልፀዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተካፈሉ ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የሰሯቸው ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ባላቸው እውቀት እና አቅም ድጋፍ እንደሚያደርጉም ነው የገለጹት።

የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን የለውጥና የብልጽግና ፓርቲን በመደገፍ ሰልፍ ያካሄዱ ሲሆን፥ በሰልፉ ላይ የፍቼ ከተማ ነዋሪዎችን ጨምሮ ከዞኑ 13 ወርዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ የህብርተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

ነዋሪዎቹ በፍቼ ስታዲየም በመገኘት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን እንደሚደግፉ እና ለብልጽግና ፓርቲም ያላቸውን ድጋፍ ገልፀዋል።

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን በሚገኙት ሱሉልታ ከተማ እና ሰንዳፋ በኬ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎችም በሀገሪቱ እየተካሄደ ላለው የለውጥ ስራ እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የድጋፍ ሰልፍ አካሂደዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ፊቼ ከተማም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይን፣ መላውን የለውጥ አመራር እና ብልጽግናን ለማበረታታት ያለመም የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።

በባሌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎችም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና ለብልፅግና ፓርቲ ድጋፍ የድጋፍ ሰልፎች ተካሂደዋል።

በሰልፎቹ ላይም “ኦሮሞ በማንኛውም ሴራ አይበታተንም፣ የህዝብ ተጠቃሚነት በፍላጎት እና በምኞት ብቻ ከግብ አይደርስም፣ በሀይማኖት እና በብሄር ሊከፋፍለን የሚፈልጉ ሀይሎች ቦታ የለንም፣ ዶክተር ዐቢይ ሁሌም የኦሮሞ ህዝብ ከጎንህ ነው፣ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ቀጣይ ጊዜ ብሩህ ነው እና ይቅርታ፣ ፍቅርና ብልፅግና ነው የሚያሻግረን” የሚሉ መልእክቶችን ተላልፈዋል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.