Fana: At a Speed of Life!

ሀዋሳና ወሎ ዩኒቨርስቲዎች ከ10 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀዋሳና ወሎ ዩኒቨርስቲዎች  በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን ከ10 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት አስመርቀዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 6 ሺህ 263 ተማሪዎች ነው በዛሬው ዕለት ያስመረቀው፡፡

ከተመራቂዎቹ መካከል 34 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።

ከተመራቂዎቹ መካከል 6ቱ በዶክትሬት ዲግሪ፣ 514ቱ በማስተርስ ዲግሪ እንዲሁም 5626ቱ ደግሞ በመጀመሪያ ዲግሪ ለመመረቅ በቅተዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ በምረቃ ሰነ ስርአቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር በኮሮናና በተለያዩ ምክንያቶች ለወራት ተጓቶ የነበረው የምረቃ መርሃግብር ዛሬ በዚህ መልኩ በመከናወኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

የእለቱ የክብር እንግዳ የሲዳማ ክልል መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ባስተላለፉት መልዕክት ሀገርን ወደፊት ለማሻገር ትምህርት ትልቅ ሚና እንዳለው በማንሳት የዛሬ ተመራቂዎችም የዚሁ አካል ናቸው ነው ያሉት።

ተመራቂዎች ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በቅንነት እንዲያገለግሉ ማሳሰባቸውን ከደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በተመሳሳይ የወሎ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 4 ሺህ 200 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት ለ12ኛ ጊዜ ባካሄደው የምርቃት ፕሮግራም አስመርቋል፡፡

በምረቃ ስነስርዓቱ ታድመው ለተመራቂዎች መልዕክት ያስተላለፉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ የተማሪዎች ምረቃ በዓል በዓለም አቀፍ ችግር በሆነው የኮቪድ 19 ወረርሽኝና በኋላም ክህደት በፈፀመው ቡድን ምክንያት በተፈጠሩ ችግሮች የዘገየ መሆኑን ገልፀው “ከመጀመሪያው በጤና ባለሙያዎች ድጋፍ ከሚደርስብን የከፋ ጉዳት ተርፈን እና ከሁለተኛው የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በከፈሉት ዋጋ ችግሩ ታልፎ ለዚህች ዕለት ተደርሷል” ብለዋል፡፡

ወረርሽኝም ይሁን ወረራ ቢያጋጥም ያለንን ሁሉ አሳባስበንና በወንድማማችነት ተሳስበን ስንቆም ያሉብንን ችግሮች መፍታትና መሻገር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያን ወደሚገባን ከፍታ ለመውጣት የሚያግደን ሃይል እንደማይኖር አሳይቶናል ብለዋል፡፡

ቀጣዩን ምእራፍ ከባለፉት ለየት የሚያደረገው  ለራሳችሁም፣ ከወላጆቻችሁና ከሀገራችሁ ሃላፊነት የምትቀበሉበት ስለሚሆን ነው ያሉት ዶክተር ሳሙኤል፡፡

እስከ ዛሬ ያነበባችሁትና ያገኛችሁት እውቀት፣ ልምምዳችሁና የቀሰማችሁት ልምድ በብዙ ምክንያት ያደገው ማስተዋላችሁ ለመጪው ከባድ ኃላፊነት በተወሰነ ደረጃ ይረዳችሁ ይሆናል እንጂ በቂ አይደለም ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳ

የፋና ድረ ቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.