Fana: At a Speed of Life!

“ሀገሬን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እቆማለሁ!” በሚል መሪ ቃል ውይይት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)”ሀገሬን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እቆማለሁ” በሚል መሪ ቃል ውይይት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ውይይቱ በአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ፅህፈት ቤት ለመከላከያ ሰራዊቱ የተዘጋጀ መድረክ ሲሆን በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ነው በመካሄድ ላይ የሚገኘው፡፡

በመድረኩ  የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንዲሁም የከተማው ሴት አመራሮች፣ የመከላከያና የፖሊስ ከፍተኛ የሴት አመራሮች የከተማው የሴት አደረጃጀቶች ተሳትፈዋል፡፡

በዚህ ወቅትም የሴት አደረጃጀቶች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ190 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ እና የምግብ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በመርሃግብሩ ላይ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት ጁንታው የህወሓት ቡድን ወደ ስልጣን ለመምጣት በርካታ ሴቶችን እና ወጣቶችን ለጦርነት በመማገድ ስልጣኑን ከያዘም በኋላ በትግል ወቅት አብረውት የነበሩትን ሴቶች ሜዳ ላይ በመተው ባለፉት 27 ዓመታት ሲበድላቸው ቆይቷል ፡፡

ይህ የጥፋት ቡድን በቅርቡም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከመፈጸም በተጨማሪ በንጹሃን ሴቶች እና ህጻናት ላይ ከባድ ሰብዓዊ ጥፋት ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

ሴቶች ሀገርን በመምራት፣ በጦር ሜዳ በግንባር በመሰለፍ የህግ የበላይነት እንዲከበር እና ፍትህ እንዲሰፍን ወሳኝ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ ያሉት ወይዘሮ አዳነች ጁንታው ጁንታውን የህወሓት ቡድን ለፍርድ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት መላው ሴቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.