Fana: At a Speed of Life!

ሀገርን ለማዳን ለተሰጠው በሳል አመራርና ሰራዊቱ ላሳየው ወደር የለሽ ጀግንነት ክብርና ምስጋና አቀርባለሁ- ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የተፈፀመውን ጥቃት በመቀልበስ ሀገርን ለማዳን ለተሰጠው በሳል አመራርና ሰራዊቱ ላሳየው ወደር የለሽ ጀግንነት ያላቸውን ክብር እና ምስጋና አቀረቡ።

15ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ማጠቃለያ ዝግጅት በዛሬው እለት በወዳጅነት አደባባይ ተካሂዷል።

በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ፣ የብሄር በሄረሰቦች ተወካዮች እና ሌሎችም እንግዶች ታድመዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የሀገሪቱን ሉአላዊነት እና የህዝቡን አንድነት አደጋ ላይ ለመጣል በሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የተከፈተውን ጥቃት ለመቀልበስ እና ሀገርን ለማዳን ለተሰጠው በሳል አመራር በሳል የጦር አመራር፣ ጥበብ እና ጥንቃቄ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት ላሳየው ወደር የለሽ ጀግንነት ምስጋና እና ክብር አቅርበዋል።

“በተለይም በንጹሃን ላይ ጉዳት ሳይደርስ ለፈጸመው ገድል እንኳን ደስ አለን ለማለት እወዳለሁ” ብለዋል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ።

መንግስት የሀገሪቱን ክብር ለመመለስ እና የፌደራል ስርዓቱን ለማስጠበቅ የወሰደው እርምጃ በስኬት እንዲጠናቀቅ ማንኛውም ልዩነት ሳያግደው በኢትዮጵያዊነት ስሜት እና በአባቶች ወኔ በአንድነት በመቆም በሚያስፈልገው ሁሉ ሁለንተናዊ ድጋፍ ላበረከተው ለኢትዮጵያ ህዝብም ያላቸውን ክበር እና ምስጋና አቅርበዋል።

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በከሃዲ ሃይሉ ለደረሰው ጥፋት፣ በሰሜን ዕዝ ላይ ለተፈጸመው ክህደት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የረጅም ዓመት የሀገርም ሆነ የመንግስት ታሪክ ያላት እንዲሁም ለዓለም በርካታ ቅርስን ያበረከተች ታላቅ አገር መሆኗን ገልጸው፤ በልጆቿ ትጋትና በመሪዎቿ አርቆ አሳቢነት ዓለም አቀፍ ተቋማት መስራች አገር መሆኗን አስታውሰዋል።

“በዚያኑ ያህልም የቆምንባቸውን ምሰሶዎች ጭምር ገዝግዘው የሚጥሉ ክፉ አጋጣሚዎችን በእኛው በራሳችን ፈጥረናል” ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ “አንዳችን በአንዳችን ላይ ግፍ ፈጽመናል” ብለዋል።

ለአብነትም ንብረት መውደም፣ ዜጎች በገዛ አገራቸው እንዲፈናቀሉ፣ እንዲፈሩና እንዲሰጉ መሆናቸውን አንስተዋል።

“ኢትዮጵያውያን መጥፎ የሚባሉ የታሪክ አጋጣሚዎችን ተሻግረናል፤ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፈናል” በማለት ገልጸው፤ ይህ ሊሆን የቻለው ከብዙ ኪሳራ በኋላ እንደሆነ መዘንጋት እንደሌለበት አስገንዝበዋል።

ባለፉት ሳምንታት የደረሰው የከሃዲዎች ጥቃት ከውጭ ጠላት የመጣ አለመሆኑን ገልጸው፤ የፈሰሰው የኢትዮጵያውያን ደም በሃዘን ላይ ሃዘን መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህ ሁኔታ አገሪቱን እየዳረገ ያለው ችግር በገጠመ ጊዜ ቆም ብሎ ከሁኔታው አለመመርመር እንደሆነም ገልጸዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህም፥ በመድረኩ ላይ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

በመልእክታቸውም ልዩነታችንን ውበት አድርገን ሀገርን ልናሻግር ይገባል ብመለዋል።

በመጨረሻም በመርሃ ግብሩ ላይ የ15ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በስኬት እንዲከበር አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትና ተሳትፎ ላደረጉ ሁሉ የምስጋና ዕውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.