Fana: At a Speed of Life!

ሁለተኛው ምዕራፍ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት በዚህ አመት ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 10 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሁለተኛው ምዕራፍ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በዚህ አመት ሊጀመር መሆኑ ተገለጸ።

ከሶስት አመት በፊት በ11 ከተሞች የተጀመረው የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሀግብር እስከዚህ አመት ድረስ በሶስት ዙር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎቸን ተጠቃሚ አድርጓል።

በሶስቱ ዙርም በእነዚህ ከተሞች 604 ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፥ ለፕሮግራሙም የዓለም ባንክ 300 ሚሊየን ዶላር የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ 150 ሚሊየን ዶላር ወጪ ማድረጋቸው ተገልጿል።

አሁን በሁለተኛው ምዕራፍ በሶስት ዙር ለሚከናወነው ፕሮግራም የዓለም ባንክ 400 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን የፌደራል የስራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጿል።

በዚህም በ72 ከተሞች የሚገኙ ከ798 ሺህ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በኤጀንሲው የከተሞች ሴፍቲኔት ዳይሬክተር አቶ አብርሀም ጴጥሮስ ተናግረዋል።

በአካባቢ ልማት ከ473 ሺህ በላይ፣ በቀጥታ ድጋፍ ከ151 ሺህ በላይ፣ እንደ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል እና ሶማሌ ባሉ ክልሎች የሚገኙ ስደተኞችን ጨምሮ ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ከ81 ሺህ በላይ እንዲሁም ስራ አጥ የሆኑ ከ70 ሺህ በላይ ወጣቶች መካተታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

በዚህም በኦሮሚያ 29፣ በአማራ 16፣ ደቡብ 12፣ ትግራይ 5፣ ሶማሌ 5፣ ሲዳማ 2፣ ጋምቤላ፣ አፋር እና ቤኒሻጉል ጉሙዝ እያንዳንዳቸው አንዳንድ ከተሞች የመርሀ ግብሩ ተጠቃሚ  እንደሚሆኑም ገልጸዋል።

በዚህኛው ምዕራፍ በመጀመሪያው ዙር ተጠቃሚ የነበሩት 11 ከተሞች በተጠቃሚነታቸው ይቀጥላሉም ነው ያሉት፡፡

ተጠቃሚ መሆን ያለባቸውን ከተሞች ለመለየትም የህዝብ ብዛት፣ የድህነት እና የስራ አጥነት ምጣኔ የሚሉ እና ሌሎች መስፈርቶች መቀመጣቸው ተገልጿል።

በዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.