Fana: At a Speed of Life!

ሁለት የአሜሪካ ሴናተሮች ሀገራቸው በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ገለልተኛ አቋም እንድትይዝ በደብዳቤ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሁለት የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተሮች አሜሪካ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ገለልተኛ አቋም እንድትይዝ በደብዳቤ ጠየቁ።

ሴናተር ኮሪ ቡከር እና ሴናተር ክርስቶፎር ኩንስ ለአሜሪካ የግምጃ ቤት ሀላፊ ስቴቨን ሙኑሸን በፃፉት ደብዳቤ ዩናይትድ ስቴትስ በህዳሴ ግድብ ላይ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል እየተደረገ ባለው ድርድር የያዘችው አቋም እንዳሳሰባቸው በመጠቆም በዚህ ድርድር ላይ ራሷን ገለልተኛ እንድታደርግ አሳስበዋል።

ሴናተሮቹ ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ተረቆ ለፊርማ የቀረበው ስምምነት ኢትዮጵያ ለግብፅ የወገነ መሆኑን በመጥቀስ አለመፈረሟን አስታውሰዋል።

ያንን ተከትሎም ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ ሲደርግ የነበረው ድርድር በስምምነት ተቋጨ አልተቋጨ ግድቡን የውሃ ሙሌት በያዘችው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንደምትሞላ መግለጿን ተከትሎ በአካባቢው ውጥረት መፈጠሩን ነው ያመለከቱት።

የግድቡ ግንባታ እየተጠናቀቀ እና የሁለቱ ሀገራት ተቃርኖ አየሰፋ በመጣበት በዚህ ወቅት ታዲያ ዩናይትድ ስቴትስ ሁኔታውን ልታበርድ ይገባል ብለዋል።

ሆኖም በጉዳዩ ላይ አሜሪካ ገለልተኛ ባለመሆኗ ይህንን ውጥረት የማብረድ ሚና መጫወት እንዳትችል እንዳደረጋት ሴናተሮቹ አስረድተዋል።

ጉዳዩ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መሄዱን ኢትዮጵያ እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በመቃወማቸው ምክር ቤቱ ጉዳዩን ለመመልከት ተመራጭ ቦታ አለመሆኑንም ነው ያመለከቱት።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለኢትዮጵያ በሁለትዮሽም ሆነ በሶስትዮሽ መንገዶች የሚደረጉ እርዳታዎች ወይም ድጋፎችን ለማገድ መንቀሳቀስ በአካባቢው ላይ በሚገኘው የአሜሪካ ብሄራዊ ጥቅም እና ፍላጎቶች ላይ በተቃራኒ መቆም መሆኑን አስጠንቅቀዋል።

ለኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ስቴትስ የሁለትዮሽ ግኝኙነት ጠቃሚነት፣ በኢትዮጵያና እና ሱዳን እየተካሄደ ያለው ሽግግር ስኬታማ መሆኑ አስፈላጊነት እና ዋሽንግተን ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ለረዥም ጊዜ ያፈሰሰችውን መዋዕለ ንዋይ እና በአካባቢው ያለን የዲፕሎማሲ ግንኙነት እና የሚደረገው እርዳታ ለአካባቢው ሰላምም ሆነ ለዩናይትድ ስቴትስ ጥቅም አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ይቁንም ከዚህ ቀደም በተደረጉ ድርድሮች ወደጎን ተገፍቶ የነበረው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እና ባለሙያዎቹ ስለ አካባቢው ጉዳይ የካበተ ልምዳቸውን ተጠቅመው ድጋፍ እንዲያደርጉ እና አሜሪካ በሶስቱም ሀገራት ተቀባይነት የሚያስገኝላትን ገለልተኛ ስፍራን እንድትይዝ ሴናተሮቹ አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.