Fana: At a Speed of Life!

ሁለት የደቡብ ክልል ዞኖችን እና የኦሮሚያ ክልልን የሚያገናኝ መንገድ እና ድልድይ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል የወላይታ ዞንን ከሀዲያ ዞን እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚያገናኝ መንገድ እና ድልድይ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡
በወላይታ ዞን በድጉና ፋንጎ ወረዳ 25 ሚሊየን ብር ወጭ የተገነባው÷ ቀርጨጨ-ደንዶ ወርቅቻ-ሆሎታ ድረስ 22 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን በዲሲ 3 ደረጃ የተገነባው መንገድ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡
መንገዱ የድጉና ፋንጎ ወረዳ ቀርጨጨ ሆሎታ ማዘጋጃን ይዞ ከሃዲያ ዞን ወረዳዎች ጋር የሚያገናኝ ሲሆን ከሌሎች ዞኖች ጋር ያለውን ወንድማማችነትን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።
መንግሥት የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ እየፈታ እንደሚገኝም በምረቃ መርሐ ግብሩ ተገልጿል፡፡
መንገዱ የትራንስፖርት አገልግሎት በማፋጠን የሚሰጠው ፋይዳ የጎላ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
የመንገዶቹ መገንባት የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም ለማረጋገጥ ሁነኛ መፍትሔ ነው ተብሏል።
የአንደኛ ደረጃ ጠጠር መንገድ ሥራው በተያዘለት ዕቅድ እንዲጠናቀቅ የክልሉን መንግስት፣ የዞኑና የወረዳ አስተዳደሮችን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ያደረጉት ድጋፍና ክትትል የሚደነቅ ነው ተብሏል።
መንገዱ በክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ በኩል በዲ ሲ 3 ስታንዳርድ የተሠራ ነው ተብሏል።
በተያያዘም በወላይታ ዞን ዛሬ ለአገልግሎት የበቃ መንገድና ድልድይን ጨምሮ 11 ሁሉ አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድና ሁለት ድልድዮች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ በወላይታ ዞን ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የመንገድና ድልድይ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
ፕሮጀክቶቹን መርቀው የከፈቱት የደቡብ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ፣ በበጀት ዓመቱ በክልሉ ለገጠር ተደራሽ መንገዶች ከ350 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተመድቦ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
ከፕሮጀክቶች መጓተት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ከመቅረፍ አኳያ በጊዜና በገንዘብ ተገድበው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ በበኩላቸው÷ ዛሬ በዞኑ ከ103 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ግንባታ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ለአገልግሎት ከበቁት ድልድዮች መካከል አንደኛው የወላይታና የሀዲያን ዞኖችን የሚያገናኝ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አክለዋል።
የድልድዩ መሰራት በወንዝ መሙላት ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን እንደሚቀንስ እና የመንገዱ መሰራት ለተለያዩ የንግድና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች መሳለጥ የሚሰጠው ፋይዳ የጎላ ነው ተብሏል፡፡
በማስተዋል አሰፋ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.