Fana: At a Speed of Life!

ሁሉም በተሰማራበት ሙያ ሀገሩን በታማኝነት ካገለገለ ወታደርም ጀግናም ነው-መቶ አለቃ አይዳ አላሮ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁሉም በተሰማራበት ሙያ ሀገሩን በታማኝነት ካገለገለ ወታደርም ጀግናም ነው ሲሉ መቶ አለቃ አይዳ አላሮ ገለጹ፡፡
 
ህወሓት በሀገር ላይ የከፈተውን ወረራ ለመመከት ከ3 ዓመት በፊት በፈቃዳቸው ወደ ለቀቁትና ወደሚወዱት የውትድርና ሙያ የተመለሱት መቶ አለቃ አይዳ አላሮ የብላቴ የልዩ ዘመቻዎች ሃይል ማሰልጠኛ ማዕከል አሰልጣኝ ናቸው።
 
“ማንም ከሀገር በላይ አይደለም” ያሉት መቶ አለቃ አይዳ ህወሀት በሀገር ላይ የደቀነውን የህልውና አደጋ ለመመከት ሲሉ ወደ አሰልጣኝነታቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።
 
“የሀገሬ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁ ከምንም በላይ ያሳስበኛል” ያሉት መቶ አለቃዋ በአሁን ሰዓት ወታደር ለመሆን የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ቁጥር ጨምሮ ሳይ ደስታዬ ወደር የሌለው ሆኗል” ብለዋል።
 
ቀደም ባሉት ዓመታት ወታደሮችን ለመመልመል ብዙ ቅስቀሳና መከራ እናይ ነበር፤ አሁን ውትድርና እንደ ሙያ የሚታይበት ክብር ያገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
 
አሁን ላይ ወታደር ለመሆን ሰራዊቱን የሚቀላቀል ዜጋ መብዛቱ ኢትዮጵያዊነት ዝም ተብሎ የሚተው እንዳልሆነና ህዝቡ በሀገር ጉዳይ እንደማይደራደር ያሳየ መሆኑን አመልክተዋል ።
 
“ኢትዮጵያዊያን ምንጊዜም ጀግኖች ናቸው” ያሉት መቶ አለቃ አይዳ “ወታደር ስትሆን በአውደ ውጊያም ሆነ በሰላም ወረዳ እንዲሁም ሲቪል ስትሆን ደሞ በተሰማራህበት ሙያ ጀግንነትን ማሳየት ግድ ይላል” ብለዋል።
 
ለሀገር ወታደር ለመሆን የግድ ዩኒፎርም መልበስና ክላሽ መታጠቅ እንደማይጠበቅ የተናገሩት አሰልጣኟ ሁሉም በተሰማራበት የሙያ መስክ ለሀገሩ በተገቢው መንገድ በቅንነትና በታማኝነት ማገልገልና ስኬታማ መሆን እስከቻለ ድረስ ወታደር ነው፤ የሚለው እሳቤ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
 
“በሲቪል ህይወቴ እንዲህ አይነት ፍቅር አላገኘሁም፤ በዚህ ቆይታዬ ያገኘሁት ፍቅር ለሀገሬ ህይወቴን በመስጠት ባንዲራዋ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲታይ ለማድረግ እሰራለሁ” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.