Fana: At a Speed of Life!

ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ከጥቅምት 23 እስከ 30 የመጀመሪያ ዙር የተማሪዎች ቅበላ እንደሚያደርጉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ከጥቅምት 23 እስከ 30 አስፈላጊውን ዝግጅት በማጠናቀቅ የመጀመሪያ ዙር የተማሪዎች ቅበላ እንዲያደርጉ አሳሰቡ፡፡

ሚኒስትሩ በቅርቡ በኮቪድ-19 ፕሮቶኮል መሠረት በተካሔደው የተቋማት ድጋፍና ምልከታ ውጤት በአንዳንድ ተቋማት የታዩ ክፍተቶች በፍጥነት ተሟልተው በግልጽ መርሃ-ግብር ለተማሪዎች ቅበላ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ሙሉ ነጋ የተቋማቱን የቅድመ ቅበላ ዝግጅት ዳሰሳ ውጤት ባቀረቡት ገለጻ ኮቪድ-19ን እየተከላከሉ የመማር ማስተማር ስራን ማስቀጠል ጥንቃቄ የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሀዋሳ እየተካሔደ ባለው የተማሪዎች ቅበላ ቅድመ ዝግጅት የማጠቃለያ ምዕራፍ የግምገማ መድረክ ላይ ኮቪድ-19 እና የሠላም ጉዳይን አስመልክቶ በተነሱት ስጋቶች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

በየደረጃው ያሉት ባለድርሻ አካላት፣ የተቋማቱ አመራሮች የበለጠ ተቀራርበው በቅንጅት በመስራት ተቋማቱ ሠላማዊ፣ ሳቢ እና የከፍተኛ ትምህርት የዓለም አቀፋዊነት ባህሪ እንዲኖራቸው እና ከማንኛውም ከተቋቋሙለት ዓላማ ጋር ካልጠጣጣሙ ጉዳዮች እንዲላቀቁ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን ዶክተር ሳሙኤል አንስተዋል፡፡

ሚኒስትሮች እና የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች በቅድመ ዝግጅት ሁኔታ ዙሪያ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ለተማሪዎቹ እና ለማህበረሰቡ ተገቢው ግንዛቤ መሰጠት እንዳለበት መገናኛ ብዙኀንም ተቋማቱም ሚናቸውን እንዲወጡ መጠየቃቸውን ከሳይንስና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.