Fana: At a Speed of Life!

ሃገረ መንግስቱ በግለሰቦች እጅ ወድቆ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሩ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 25 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሃገረ መንግስቱ በግለሰቦች እጅ ወድቆ እንደነበር ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።

በምላሻቸውም ከለውጥ በፊት ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ እንደ ሃገር መቀጠል የማትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳ እንደነበር ጠቅሰው፥ ሃገረ መንግስቱም በግለሰቦች እጅ ወድቆ እንደነበር ገልጸዋል።

መደበኛ ያልሆነው እና በጥቅም፣ በዝምድና እና በትውውቅ የተሳሰረ የመንግስት ጥልፍልፎሽ እንደነበር አስታውሰው ይህም ከለውጡ ማግስት የነበረውን የመንግስትን ስራ አደጋ ላይ ጥሎት ነበር ብለዋል።

መንግስት በወሰደው እርምጃም ሃገር ላይ የተደቀነውን አደጋ መቀነስ መቻሉንም አብራርተዋል።

በተሰራ ስራም በሃገር ውስጥ የሚገኙ እስረኞችን እና በተለያዩ ሃገራት ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ማስፈታት እና በተለያዩ ሃገራት የነበሩ ፖለቲካኞች ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እና የሚዲያ አውታሮች እንዳይዘጉ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው፥ አፋኝ ሕጎችን ለማሻሻል ጥረት መደረጉንም አንስተዋል።

ተቋማዊ ለውጥን ለማምጣት በተደረገው ጥረት እንቅፋቶች ማጋጣማቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ለነበሩ አብዛኛዎቹ ችግሮች ገዢው ፓርቲ ምንጭ እንደነበር ተናግረዋል።

ከለውጡ ማግስት እስካሁን ባለው ሂደትም የተቋም ግንባታ ሂደት ኪሳራ በማያመጣ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አውስተው፥ የሴራ እና የሽብር ፖለቲካውን በማስቆም ኢትዮጵያን ወደ ፊት እናስቀጥላለንም ነው ያሉት።

በተካሄደው የለውጥ ስራ በሀገሪቱ ለነበረው ችግር ምንጭ በነበረው ገዢ ፓርቲ ላይ ምንም አይነት ችግር ሳይፈጠር አዲሱን አስተሳሰብ እንዲሸከም በማድረግ ተስተካክሏል ብለዋል በሰጡት ማብራሪያ።

የፌደራልና የክልል መንግስታትን ግንኙነት በተመለከተ በሰጡት ምላሽ ደግሞ የፌደራል መንግስቱ፥ ክልሎቹ ድጋፍ ሲጠይቁት፣ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጸም እና ሀገረ መንግስቱ አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ወደ ክልሎች በመግባት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ጊዜያት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚገዳደሩ ሁኔታዎች እንደነበሩ ጠቅሰው፥ አል ሸባብ በኢትዮጵያ ሊፈጽም የነበረውን ጥቃት መከላከል መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በቅርቡም የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥሉ የነበሩ ተግባራት ይፋ እንደሚሆኑም አውስተዋል።

ከታገቱ ተማሪዎች ጋር በተያያዘ በሰጡት ምላሽ ለተማሪዎቹ መታገት ሃላፊነት የወሰደ አካል አለመኖሩን እና ጉዳት የደረሰበት ተማሪ መኖሩን የሚያሳይ መረጃ አለመገኘቱንም አስረድተዋል።

በድርጊቱ ሃገር፣ ህዝብና መንግስት ተጎጂ ነው፤ ጉዳዩ ውስብስብ በመሆኑ በጥንቃቄ ተይዟልም ነው ያሉት፤ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና በሰላም ሚኒስቴር የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጉዳዮን እየተከታተለ መሆኑን በመጥቀስ።

ኮሚቴው የደረሰበትን ውጤት ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ያነሱ ሲሆን፥ የታጠቀ ሃይል ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ጥቃት አለመፈጸሙንና ተማሪዎቹ በማንነታቸው አለመታገታቸውንም አንስተዋል በምላሻቸው።

ወለጋ አካባቢ ካለው ሁኔታ ጋር በሰጡት ምላሽም መንግስት ሁኔታውን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፤ በአንድ ሃገር ሁለት መንግስት ስለማይኖር ህጋዊው መንግስት ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን ክፍተትን በመሙላት በሰላማዊ መንገድ መወያየት እና ወደ ሰላም መምጣት ማሸነፊያ መንገድ ነው፤ ወንድም ወንድሙን አይገልም ብለዋል።

ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ጋር በተያያዘ ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ከ1980 ጀምሮ ላለፉት 20 ዓመታት 287 የመንግስት ድርጅቶች ወደ ግል መዘዋወራቸውንና ከለውጡ በኋላ ወደ ግል የተዘዋወረ ተቋም እንደሌለም ነው የተናገሩት።

በአመቱም በ190 ቢሊየን ብር 150 ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆኑንም ነው ያነሱት።

የባንኩ ዘርፍ ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ ሆኗል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችን አቅም ለማሳደግና ኢኮኖሚውን ለመደገፍ ያስችላልም ነው ያሉት በማብራሪያቸው።

በቴሌኮም ዘርፍ የዋጋ ቅናሽ መደረጉን አውስተው የተጠቃሚዎች ቁጥርም ሆነ የተቋሙ ገቢ ማደጉንም ጠቅሰዋል።

የውሃ ሃብት የኢትዮጵያ ዋነኛ የኃይል ምንጭ እንደመሆኑ መጠን ለውሃ ሃብት ትኩረት እንደሚሰጥም አብራርተዋል።

የትግራይ ህዝብን ያገለለ አካሄድ ይስተዋላል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም የትግራይን ህዝብ ያገለለ መንግስት እንደማይፈጠር ጠቁመው፥ ህዝቡ ያለው የካቢኔ ውክልና ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ስለመሆኑም ነው የገለጹት።

ከዚህ ባለፈ ግን ከውጭ ሃገራት ጋር የሚኖረው የዲፕሎማሲ ግንኙነት የፌደራሉ መንግስት ስልጣን ስለመሆኑም አስረድተዋል።

ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘም እስካሁን በተሰራው ስራ እና በተወሰነው ውሳኔ አበረታች ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።

ከቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያ መንግስት ምርጫው እንዲካሄድ ፍላጎት ቢኖረውም ምርጫ ቦርድ ወሳኙ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጅ ከመንግስትና ምርጫ ቦርድ ባለፈም ህብረተሰቡና ፖለቲከኞች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አንስተዋል።

የህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ የማዕድን፣ ወርቅ እና ሌሎች ድርጊቶችን ለመከላከል መንግስት ስራዎችን ሲያከናውን እንደቆየ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በዚህም 14 ኪሎ ግራም ወርቅ እንዲሁም 22 ሚሊየን ዶላር መያዙን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህም ለብሄራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን ገልፀዋል።

ከሃገር ውስጥ ገንዘብ በማሸሽ በውጭ ሃገራት ባንኮች ተቀማጭ የሆኑ ገንዘቦችን ለማስመለስ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ ነው፤ ውጤት ሲገኝም በዝርዝር ይቀርባል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ነገር ግን ከሀገር የሸሸ ገንዘብን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት ገንዘቡ የሚገኙባቸው ባንኮች ሀገራት የባንኮቻችንን ጥቅም ይጎዳብናል በሚል ስራውን ለመፈፀም ለመንግስት አዳጋች እንደሆነ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወቅት የተያዘው ንብረት ለብሄራዊ ባንክ ገቢ እንደተደረገ መረጃ እንዳላቸው እና ገቢ ያልተደረገ ካለም መረጃውን ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ ማጣራት እንደሚቻል አብራርተዋል።

ከቦንጋ ከተማ የውሃ እና ሆስፒታል ችግር ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄም አሁን ላይ ሁለት ኮሚቴዎች ተዋቅረው ምላሽ በመስጠት ላይ እደሚገኙ አንስተዋል።

ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ እየተካሄደ የሚገኘው ድርድር ሳይጠናቀቅ ጥቅማችንን አጥተናል እና ተጠቅመናል በሚል መደምደም ከባድ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ እያካሄዱት የሚገኘው ድርድር ላይ ኢትዮጵያ ጥቅሟን የሚነካ ተግባር እንደማትፈፅምም አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሜሪካ እና የዓለም ባንክ በድርድሩ ወቅት በታዛቢነት በመሳተፋቸው መልስ ሳያገኙ የቆዩ ጉዳዮች መልስ ማግኘት ጀምረዋል ነው ያሉት።

ድርድሩ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ በሚያደርግ እና ዘላቂ ሰላምን በሚያሰፍን መልኩ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በግማሽ ዓመቱም ለ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን የገለፁ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 65 በመቶ በቋሚነት እና 35 በመቶ በጊዜያዊነት መሆኑንም አንስተዋል።

የአንበጣ መንጋን በተመለከተ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህም ብዙ ጉዳቶችን መቀነስ እንደተቻለ ነው የገለፁት።

 

በምናለ ብርሃኑ እና ኤፍሬም ምትኩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.