Fana: At a Speed of Life!

ህወሃት የዘረጋው ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ኔትዎርክ ከነተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27 ቀን 2013 አሸባሪው የህወሃት ጁንታ ቡድን ከአዲስ አበባ እስከ ቶጎ ውጫሌ በዘረጋው ህገ-ወጥ የዶላርና የገንዘብ ዝውውር ኔትዎርክ ሲጠቀምባቸው የነበሩ ሰነዶችና ገንዘቦች ከነተጠርጣሪዎቹ መያዙን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለፀ፡፡
 
ዶላሩ ከአዲስ አበባ በጥቁር ገበያ እየተሰበሰበ መንግስትን እንዲዳከም ሲሰሩ የተደረሰባቸው መሆኑን ነው የተገለጸው፡፡
 
አሸባሪው ቡድን ቀድሞ በሰራው ኔትዎርክ አማካኝነት በንግድ ተቋማት የሚሰበሰቡትን ዶላሮች በሀገ-ወጥ መንገድ ከሀገር እንዲወጣ በማድረግ ለሽብር ቡድኑ ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
 
ከወንጀል ድርጊቱ ጋራ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርገዋል ያላቸውን 6 አለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችና 11 ግለሰቦች ከ14 ባንኮች የተከፈቱና አስር ሚሊዮን ሁለት መቶ ሰባ ስድስት ሺህ አራት መቶ ዘጠና ስድስት ብር ከያዙ ከመቶ በላይ የባንክ ቡኮች ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ጁንታው በአዲስ አበባ ህጋዊ አሰራርን ሽፋን በማድረግ መንግስት እንዲዳከምና ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስገባቸው ጥሬ እቃዎች የዶላር እጥረት እንዲያጋጥመው እንዲሁም የኑሮ ውድነትን አባብሶ ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳ ለማድረግ የሞከረ መሆኑንም ድርሼበታለሁ ብሏል፡፡
 
አሸባሪ ቡድኑ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ደጋፊዎቻቸው ገንዘብ በመሰብሰብ ለጦር መሳሪያ ግዥና ለባለስልጣናት ልጆች ትምህርት ቤት ወጪ ያውሉታል ተብሏል።
 
የሽብር ቡድን በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ማድረጋቸውም ተነግሯል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.