Fana: At a Speed of Life!

ህወሃት ጊዜው እየመሸበት ሲሄድ የትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ መስሎ ቀርቧል – የትግራይ ተወላጆች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ህወሃት ጊዜው እየመሸበት ሲሄድ የትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ መስሎ መቅረቡን በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ገለጹ።

የትግራይ ተወላጆች እንደገለጹት ቡድኑ ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት ሲገዛ በአገርና ህዝብ ላይ የፈፀመው ግፍና በደል በርካታ ነው ብለዋል።

በእነዚህ ዓመታት ለራሱ ህልውና እና አብረውት ለቆሙት ቡድኖች ከመጥቀም ውጭ ለትግራይ ህዝብ “እዚህ ግባ” የሚባል ጥቅም እንዳላስገኘለትም ነው የተገለጸው።

ሆኖም የጥፋት ቡድኑ አሁን ላይ “ጊዜው እየመሸበት” ሲሄድ የትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ መስሎ ለመቅረብ መሞከሩን ገልጸዋል።
የትግራይን ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ለነፍሱ ማቆያ ለማድረግ የጥፋት መልዕክተኛ ማድረጉ ደግሞ የህወሃትን ፍፁም የሆነ ግለኝነት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ሙዑዝ ገብረ ህይወትና ወይዘሮ መሰሉ ረዳ የተባሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዳሉት ህወሃት የትግራይን ህዝብ ሊወክል የማይችል የጥፋት ቡድን መሆኑን ነው የጠቀሱት።

ቡድኑ በአገር ላይ ክህደት በመፈፀም የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመው አሳፋሪ ድርጊት መሆኑን ገልጸው የወንጀሉ ተሳታፊ በሆኑ የምክር ቤት አባላት ላይ ያለመከሰስ መብታቸው መነሳቱም ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

የትግራይ ወጣት ጊዜው የመሸበትን የህወሃት ቡድን በመታገል ለህግ እንዲቀርብ የመከላከያ ሃይሉን እንዲያግዝም ጠይቀዋል።

የህወሃት ጁንታ የራሱን ልጆችና ዘመዶች በተለያዩ የዓለም አገራት እያኖረ የድሃውን ህዝብ ልጅ ከትምህርት እያቋረጠ የአገር መከላከያ ሰራዊትን እንዲወጋ ማሰለፉ በወላጆችም ይሁን በወጣቶቹ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።

የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት ጁንታውን “እምቢ” በማለት እጃቸውን ለአገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሰጡም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የህወሃት ጁንታ በህግ ማስከበሩ ሂደት በቁጥጥር ስር ውሎ በጦር ፍርድ ቤት ሊዳኝ ይገባዋልም ነው ያሉት ነዋሪዎቹ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.