Fana: At a Speed of Life!

ለሀገር ህልውና እየተደረገ ያለው ድጋፍ አቅም የሌላቸውን ወገኖች በማገዝ እንዲደገም ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህልውና ዘመቻው ሀገርን ለማዳን በቅንጅት እየተደረገ ያለው ድጋፍ አቅም የሌላቸውን ወገኖች አግዞ በማሻገር ሊደገም እንደሚገባ ተመለከተ።
የኢትዮ-ቴሌኮም ምስራቅ ሪጅን ጽህፈት ቤት በድሬዳዋ አስተዳደር 23 የከተማና ገጠር ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ 1ሺህ 500 አቅም የሌላቸው ተማሪዎች በነፍስ ወከፍ አንድ ደርዘን ደብተር አበርክቷል፡፡
የድጋፍ ርክክቡ በተካሄደበት ወቅት የሪጅኑ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ጣሰው ሽመልስ፤ “ተማሪዎች በደብተርና ምግብ እጥረት ከትምህርታቸው እንዳይለዩ ሁሉም ሊደግፋቸው ይገባል” ብለዋል፡፡
በትምህርት ላይ የሚደረግ ድጋፍ ሀገር ገንቢና ተረካቢ ትውልድን መገንባት በመሆኑ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉአስታውቀዋል፡፡
በድጋፍ ርክክቡ ስነ-ስርዓት የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሀመድ በበኩላቸው፤ “በአሁኑ ወቅት ሀገርን ለማዳን እየተደረገ ያለው ርብርብ አቅመ ደካሞችን በማገዝ ሊደገም ይገባል” ብለዋል፡፡
ችግረኛ ተማሪዎች በትምህርት መረጃ ቁሶች እጥረት ከትምህርት ገበታ እንዳይቀሩ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ተናግረው፣ ኢትዮ-ቴሌኮም ያደረገው ድጋፍ በአርአያነት እንደሚጠቀስ ገልጸዋል፡፡
በድሬዳዋ የገንደ አዳ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሰኢድ ዚያድ ሱሌይማን የተደረገለት ድጋፍ በትምህርቱ ጠንክሮ ለመማር እንደሚያግዘው ነው የተናገረው፡፡
ዘንድሮ ኢትዮ-ቴሌኮም በ16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የገዛቸውን 600ሺህ ደብተሮች በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ 50 ሺህ ተማሪዎች እንደሚያከፋፍል ታውቋል።
በተመሳሳይ የድሬዳዋ ገቢዎች ባለስልጣን የጤና እግር ኳስ ቡድን አስተባባሪነት አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የሚውሉ የመማሪያ ቁሶች ድጋፍ ተደርጓል።
ቡድኑ “አንድ ደርዘን ደብተር፥ለአንድ ችግረኛ ህጻን ” መሪ ሀሳብ ት ከድሬዳዋ ነዋሪዎች ግምታቸው ከ800 ሺህ ብር በላይ የሆኑ ደብተሮች፣ እስክሪፕቶዎች፣ ጫማ፣ የደንብ ልብስና ሌሎች የመማሪያ ቁሶችን አሰባስቦ ዛሬ ለትምህርትቢሮ አስረክቧል፡፡
የትምህርት ቢሮው የተረከባቸውን የትምህርት ቁሶች በ16 ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ 1ሺህ 400 ችግረኛ ተማሪዎች እንደሚከፋፈሉ ታውቋል፡፡
የባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልሰላም መሐመድ ” ተማሪዎች በምግብ ችግርም ከትምህርት ገበታቸው እንዳይለዩ በሚደረገው ጥረት አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል” ብለዋል፡፡
በድጋፍ ርክክቡ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈጡም ሙስጠፋና የካቢኔ አባላት ለተደረገው ድጋፍም ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.