Fana: At a Speed of Life!

ለልዩነት ሳይሆን ለአንድነት አጽንኦት መስጠት አለብን-ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ”ከልዩነታችን ይልቅ ለአንድነታችን፣ ከባለፈው ይልቅ ለአሁኑ አጽንኦት መስጠት ይጠበቅብናል” ሲሉ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበርና በፍሬድሪክ ኤበርት ፋውንዴሽን ትብብር የተዘጋጀ አውደጥናት “ትስስርና መስተጋብር በኢትዮጵያ ታሪክ” በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።

በመድረኩ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፣ የሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፣ የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንዲሁም በተለያዩ የትምህርት ተቋማት የሚሰሩ ምሁራን ተገኝተዋል።

ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በዚሁ ወቅት÷ ኢትዮጵያ ረጅምና ደማቅ ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው÷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታሪክ የፖለቲካ ግብግብ አውድማ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

ይህም በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና አለመግባባቶች እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቁመው÷ በ1983 ዓ.ም የተደረገው የስርዓት ለውጥ መፈክሩ “ህብረ ብሔራዊ አንድነት” ወይም “አንድነት በብዝሀነት” ቢሆንም አንድነቱ ሳይሆን ብዝሀነቱ ገኖ ወጥቷል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን በብዙ መንገድ እርስ በእርስ የተሳሰሩና የተጋመዱ መሆናቸውንም አንስተዋል።

በህብረ ብሔራዊ ትስስር የተሞላው የታሪክ ሀቅ በተለይም ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እንቅስቃሴ በተጀመረበት በአሁኑ ወቅት ጎልቶ ሊወጣ ይገባልም ነው ያሉት።

ማህበሩ ከተቋቋመበት አላማ አንዱ ታሪክና የታሪክ ትምህርት ለብሔራዊ መግባባት ስለሚውልበት ሁኔታ ሙያዊ አስተዋጽኦ ማበርከት መሆኑን ኢዜአ በዘገባው አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.