Fana: At a Speed of Life!

ለመኸር እርሻ ለአግሮ ኬሚካል ግዢ ከ60 ሚሊየን ዶላር በላይ ተመድቧል – የግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 2 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2014/2015 የመኸር ምርት ዘመን የአግሮ ኬሚካል እጥረት እንዳይከሰት ከ60 ሚሊየን ዶላር በላይ በጀት ተመድቦ በግዥ ሂደት ላይ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ እንደገለጹት ÷ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተለይም የአግሮ ኬሚካል ግብአት ወሳኝነት አለው።

በመሆኑም በ2014/2015 የመኸር ወቅት የሚያስፈልገው የአግሮ ኪሚካል ግብዓት በክልሎች ፍላጐት መሰረት ቀደም ብሎ ግዥ መፈጸሙን ገልጸዋል።

ለተያዘው የመኸር ወቅት የአግሮ ኬሚካል እጥረት ሊገጥም ይችላል በሚል ስጋት በመንግስት ከ60 ሚሊየን ዶላር በላይ በጀት ተይዞ በግዥ ሂደት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽንና በኦሮሚያ ፌዴሬሸን በኩል ግዥው እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በአጠረ ጊዜ ለተጠቃሚዎች እንዲሰራጭ ይደረጋል ብለዋል።

በዘንድሮው የምርት ዘመን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማዳበሪያ ዋጋ በመናሩ አይደርስም የሚል ስጋት የነበረ ቢሆንም፥ በቅንጅታዊ ስራ ከተገዛው 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ 96 በመቶው ሀገር ውስጥ ገብቶ መሰራጨቱንም ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከቀናት በፊትም ለአርሶ አደሩ ቡቃያ ዕድገት የሚያገለግለው 50 ሺህ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ የጫነች መርከብ ጅቡቲ ደርሳ ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት ስራ እየተሰራ መሆኑም ተዘግቧል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.