Fana: At a Speed of Life!

ለተሰንበት ግደይ የ5 ሺህ ሜትር ክብረወሰንን በማሻሻል አሸነፈች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለተሰንበት ግደይ ስፔን ቫሌንሺያ በተካሄደው የ5 ሺህ ሜትር ውድድር ክብረወሰን በማሻሻል አሸነፈች፡፡

የ22 ዓመቷ ለተሰንበት ርቀቱን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 14 ደቂቃ ከ6 ሰከንድ ከ62 ማይክሮሰከንድ ነው፡፡

ይህን ተከትሎም በሌላኛው ኢትዮጵያዊት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ተይዞ የነበረውን የሴቶች የ5 ሺህ ሜትር ክብረ ወሰን አሻሽላዋለች፡፡

ከዚህ ቀደም ከ12 ዓመታት በፊት በ14 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ ከ15 ማይክሮሰከንድ በሆነ ጊዜ ጥሩነሽ ዲባባ የርቀቱ ክብረ ወሰን ባለቤት እንደነበረች  ይታወሳል፡፡

ለተሰንበት ማሸነፏን ተከትሎ በሰጠችው አስተያየት የረጅም ጊዜ ህልሟ እንደነበር ጠቅሳ በማሸነፏ መደሰቷን ገልጻለች፡፡

በሌላ በኩል ዑጋንዳዊው ጆሽዋ ቼፕቴጌ በወንዶች 10 ሺህ ሜትር ርቀት የአትሌት ቀነኒሳ በቀለን ክብረወሰን በማሻሻል አሸንፏል፡፡

የ24 ዓመቱ ጆሽዋ ርቀቱን 26 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ በሆነ ጊዜ ነው ማጠናቀቅ የቻለው፡፡

በዚህም ከ15 ዓመታት በፊት በቀነኒሳ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን በስድስት ሰከንዶች ለማሻሻል በቅቷል፡፡

ጆሽዋ በ10 ወራት ውስጥ አራት ክብረወሰኖችን ያሻሻለ ሲሆን ከዚህ ቀደም በቀነኒሳ ተይዞ የነበረውን የ5 ሺህ ሜትር ክብረወሰን በሁለት ሰከንዶች ማሻሻሉን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.